በአዲስ አበባ የተከናወኑ የትምህርት ሪፎርሞች የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገሩ ነው

You are currently viewing በአዲስ አበባ የተከናወኑ የትምህርት ሪፎርሞች የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገሩ ነው

AMN – መስከረም 5/2019 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትምህርት ዘርፍ የተከናወኑ አዳዲስና ሰፊ የሪፎርም ሥራዎች የተማሪዎችን ውጤት ከማሻሻል ባለፈ፣ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገሩ ይገኛሉ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ትውልድ ከማፍራት አኳያ የሰጠው ልዩ ትኩረት አሁን ላይ ተጨባጭና አስደሳች ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።

በከተማ ደረጃ የተማሪዎችን ውጤትና የትምህርት ጥራት በአግባቡ እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

ለአብነትም ከ1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ጥራት ያለው ምገባ በመሰጠቱ፣ ተማሪዎች በምግብ ሳቢያ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ መደረጉ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡

ይህ የምገባ መርሃ ግብር ተግባራዊ መደረጉ ተማሪዎች ሰዓት አክብረው እንዲገኙና ትኩረታቸውን ሙሉ በሙሉ በትምህርታቸው ላይ እንዲያደርጉ ከማስቻሉም በላይ፣ ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እናቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

በሁሉም የትምህርት እርከኖች የመጻሕፍት እጥረት እንዳይኖር ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት በክረምት ወቅት መሰራጨቱ ለተማሪዎች የውጤት እና የትምህርት ጥራት መሻሻል አበርክቶው ከፍተኛ ነው፡፡

በተጨማሪም የደብተር እና የዩኒፎርም አቅርቦት መሟላቱ ለመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ ሁኔታን በተለይም በክረምት ወቅት በተመረጡ ክላስተር ማዕከላት ለተማሪዎች የሚሰጡ የማጠናከሪያ ትምህርቶች ተማሪዎች ለፈተና በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉና ውጤታቸው እንዲያድግ ትልቅ አቅም ፈጥረዋል።

በሕብረተሰቡ አጠቃላይ ተሳትፎና በከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ 13 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት ተሰብስቦ ትምህርት ቤቶች እንዲታደሱና በቂ ግብዓት እንዲሟላላቸው መደረጉ የመማሪያ አካባቢውን ለተማሪዎች ምቹ ተደርጓል፡፡

የልዩ ፍላጎት ማዕከላት ቁጥር ወደ 124 ከፍ ማለቱ፣ የብሬል መጻሕፍት መታተማቸው እና አስፈላጊ የድጋፍ መሣሪያዎች መሟላታቸው ትምህርትን ፍትሐዊና አካታች በማድረግ የሁሉም ተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ማድረጉን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያሳያል፡፡

በተጨማሪም የትውልድ ድምጽ በሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ኤ.ኤም.ኤን ፕላስ (AMN+) ላይ የሚተላለፉ የቴሌቪዥን ትምህርቶች እና የዲጂታል መድረኮች ተማሪዎች ተጨማሪ ትምህርት እንዲያገኙና እውቀታቸውን እንዲያዳብሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

እነዚህ የተቀናጁ የልማትና የሪፎርም ሥራዎች የነገዋን ኢትዮጵያ በዕውቀትና በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማስረከብ የተጀመረው ትልቅ ምዕራፍ ማሳያዎች ናቸው፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review