AMN – መስከረም 4/2019 ዓ.ም
በህንድ ኒው ደልሂ የተካሄደው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ በስኬት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በጉባኤው ላይ የተሳተፉት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው ለሀገራቱ የጋራ ዕድገት ካበረከቱት አስተዋጽኦ ጎን ለጎን በርካታ አበይት ሀገራዊ ጉዳዮችን አሳክተው ተመልሰዋል።
መስከረም 3 ቀን 2019 ዓ.ም ‘‘ጽናትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርን እና ዘላቂነትን መገንባት’’ በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደው የጉባኤው ሁለተኛ ቀን፣ ጥምረቱ 140 የጋራ አቋሞችን የያዘ የኒው ዴልሂ መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በጉባኤው ዋና ዋና ድሎችን አስመዝግባለች፡፡ለአብነትም፡-
ጥምረቱ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የንግድ ድርጅት ለመቀላቀል እያደረገች ያለውን ሁለገብ ጥረት በጽኑ እንደሚደግፍ በድጋሚ አረጋግጧል።
በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ምክር ቤት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ብቸኛ እጩ በመሆን ተጨማሪ መቀመጫ እንድታገኝ የሚደረገውን ጥረት አባል ሀገራቱ በአንድነት እንደሚደግፉ የወጣው የአቋም መግለጫ አመላክቷል።
ሀገሪቱ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኮፕ 32 በባለቤትነት ለማዘጋጀት የጀመረችውን ተነሳሽነትና ዝግጅት የብሪክስ አባል ሀገራት እንደሚደግፉ በጋራ መግለጫቸው አረጋግጠዋል።
ሌላው ከዋናው መድረክ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአባልና አጋር ሀገራት መሪዎች ጋር ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይቶችን አካሂደዋል። በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በመከላከያ መስኮች ትብብር፣ እንዲሁም በዲጂታላይዜሽን ዙሪያ ሊኖሩ ስለሚችሉ የትብብር መስኮች በጥልቀት ተወያይተዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ ድሎችን ያገኘችበት የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ
መስከረም 4/2018 ዓ.ም
‘‘ጽናትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርን እና ዘላቂነትን መገንባት’’ በሚል መሪ ቃል የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት መሪዎች እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች የተሳተፉበት የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ተጠናቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው ለሁለት ቀናት በተካሔደው የ18ተኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተሳተፉ ሲሆን ፣ ጥምረቱ 140 የጋራ አቋሞችን የያዘ የኒው ዴልሂ መግለጫንም አዉጥቷል፡፡
የአቋም መግለጫዉ የዓለም አቀፍ አስተዳደር ማሻሻያ፣ ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ሰላም፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትሥሥርን ያካተቱ ዐበይት ጉዳዮች ላይ የአባል ሀገራቱን የጋራ አቋም ያንጸባረቀ ነዉ፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የንግድ ድርጅት ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት ጥምረቱ በጽኑ እንደሚደግፍ ጉባዔዉ በድጋሚ አረጋግጧል፡፡
በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ምክር ቤት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ብቸኛ እጩ በመሆን ተጨማሪ መቀመጫ እንድታገኝ የሚደረገውን ጥረት በጽኑ እንደሚደግፍም ጨምሮ አመላክቷል።
ጉባዔተኞቹ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኮፕ 32 ለማዘጋጀት የጀመረችውን ተነሳሽነትና ዝግጅት እንደሚደግፉም በጋራ መግለጫቸው አረጋግጠዋል።
ጥምረቱ 19ኛውን የብሪክስ ጉባኤ በቻይና አስተባባሪነት እንዲዘጋጅም በጋራ አጽድቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከመሪዎቹ ጉባኤ ጎን ለጎን ከአባልና አጋር ሀገራት መሪዎች ጋር በሁለትዮሽ የሀገራቱ ትብብር ዙሪያ ፍሬያማ ውይይቶችን አካሄደዋል፡፡
በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በመከላከያ መስኮች ትብብር፣ በዲጂታላይዜሽን ዙሪያ ሊኖሩ ስለሚችሉ ትብብሮች በጥልቀት ተወያይተዋል።
በድኅረ ጉባኤዉ ለመሪዎች በተደረገው የእራት ግብዣ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከተለያዩ የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት መሪዎች ጋር የታደሙ ሲሆን፤ የሁለት ቀናት የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤን አጠናቅቀው መመለሳቸዉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡