AMN- መስከረም 3/2019 ዓ.ም
የብሪክስ ሀገራት መሪዎች “ለጽናት፣ ለፈጠራ፣ ለትብብር እና ለዘላቂ ልማት መገንባት” በሚል መሪ ቃል በህንድ ኒውዴልሂ ከተማ ያካሂዱትን 18ኛውን ጉባኤ አጠናቀዋል።
ጉባኤው ባወጣው የአቋም መግለጫ፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያን ሚናና ተሳትፎ የሚያጠናክሩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በመግለጫው፤ የብሪክስ አባል ሀገራት ኢትዮጵያና ኢራን ወደ ዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባልነት ለመቀላቀል እያደረጉት ያለውን ጥረት እና ፍላጎት በጥብቅ እንደሚደግፍ አረጋግጧል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ድጋፍ የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ምክር ቤት ተጨማሪ መቀመጫዎችን ለመረከብ ብቸኛ የአፍሪካ እጩ ሆና መመረጧ ተመላክቷል።
በድርጅቱ 43ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለሚካሄደው ምርጫም ኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ ድጋፍ ተችሯቸዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ለሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት (COP32) ፕሬዚዳንትነት እንደምትረከብ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ለዚህ አዲስ ኃላፊነት ጠንካራ ድጋፍ እንደሚሰጥ በመግለጫው ተመላከቷል።
መሪዎቹ በጋራ መከባበር፣ ሉዓላዊ እኩልነት፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትህ እና አካታችነት ላይ የተመሰረተውን የብሪክስ ትብብር በፖለቲካና ፀጥታ፣ በኢኮኖሚና ፋይናንስ፣ እንዲሁም በባህልና ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ምሰሶዎች ለማጠናከር ቃል ገብተዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን (ተመድ) ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይበልጥ ዴሞክራሲያዊ እና ታዳጊ ሀገራትን ያካተቱ እንዲሆኑ፣ በተለይም የዩኤን ሴኪዩሪቲ ካውንስል ማሻሻያ እንዲደረግበት ጥሪ ቀርቧል።
አፍሪካን ጨምሮ ታዳጊ ክልሎች በዓለም አቀፍ ውሳኔ ሰጪ አወቃቀሮች ውስጥ ትርጉም ያለው ውክልና እንዲኖራቸው አጽንኦት ተሰጥቶበታል።
በኢኮኖሚው መስክም አይ ኤም ኤፍ፣ የዓለም ባንክ እና የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) ታዳጊ ሀገራትን ድምጽ በሚያረጋግጥ መልኩ ሊሻሻሉ እንደሚገባ ተመላክቷል።
በበረከት ጌታቸው