AMN- መስከረም 5/2019 ዓ.ም
በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ፣ ብቃት ያለውና አገር ተረካቢ ትውልድ ለመቅረፅ የተጀመሩ የለውጥ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት ማሳየት መጀመራቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለፁ።
ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ፤ የትምህርት መሰረተ ልማትን ለማሻሻል በተጀመረው ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ እና የትምህርት ስርዓት ሪፎርሞች አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
የለውጡ ዋና ዓላማ ከቅድመ-መደበኛ፣ ከ1ኛ ደረጃ እና ከ2ኛ ደረጃ ጀምሮ በራስ መተማመን ያለው፣ ጥራትና ሙሉ አቅም ያለው አዲስ ትውልድ መገንባት መሆኑንም አንስተዋል።
የሪፎርሙ ውጤት በሂደት እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት የትምህርት ጥራት እየተሻሻለ መምጣቱንና ትክክለኛ አቅም ያላቸው ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እየገቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም በአገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ላይ የተደረገው የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም የተማሪዎችን ውጤትና አጠቃላይ የትምህርት ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለው መምጣቱን ገልፀዋል።
በቀጣይም ተማሪዎች ከዚሁ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን የቴክኒክና ሙያ ትምህርቶችንም ጭምር እንዲያስተምሩ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከናወነው የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ አማካኝነት በገንዘብና በአይነት በርካታ ሀብት ከህብረተሰቡና ከባለድርሻ አካላት መሰብሰቡን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ይህ ንቅናቄ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የመንግሥት ጥረት ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡና የወላጆች ንቁ ተሳትፎ የታየበት ትልቅ እርምጃ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዚህም ወደ 17 ሺህ የሚጠጉ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን፤ ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ዕድሳት ተደርጎላቸው ለ2019 በጀት ዓመት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች በመገንባታቸው የተማሪዎችን መጨናነቅ መቀነሱን ተናግረዋል፡