AMN- መስከረም 5/2019 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚተገበረው የተማሪዎች ምገባ አገልግሎት በትምህርት ጥራት ማሻሻልና በማህበራዊ ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ እያበረከተ ይገኛል፡፡
በመዲናዋ ከሚከናወኑ ሰው ተኮር ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው የተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ እንዲሁም የወላጆችን ኢኮኖሚያዊ ጫና በማቃለል ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
መርኃ ግብሩ ከተማሪዎች መሰረታዊ የምግብ ፍላጎት ማሟላት ባለፈ በማህበራዊ ህይወትም ላይ በጎ ተጽዕኖ እያበረከተ ነው፡፡
የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎቱ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተገቢው ሁኔታ እንዲከታተሉም አድርጓል፡፡
እንዲሁም የተማሪዎችን በክፍል ውስጥ የመረዳት አቅም እያሻሻለ ሲሆን ለአዕምሯዊና አካላዊ እድገታቸው አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በተመሳሳይ የተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ለእናቶች እና ለወጣቶችም የሥራ ዕድልን ፈጥሯል፡፡
የተማሪዎች የምገባ መርኃ ግብር ብቁ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት ትልቅ አቅም እየሆነ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ምገባ ኤጀንሲ መረጃ ያመላክታል፡፡
በ2019 የትምህርት ዘመን በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ስርዓተ ትምህርት ተቀርፆ የነገ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ለመቅረጽ እየተሠራ ይገኛል፡፡
በከተማዋ ልጆች አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ እያሉ ተጨማሪ ክህሎት ይዘው እንዲያድጉ እየተሰራ ሲሆን ይሄም በተማሪዎች ላይ አበረታች ለውጥ እያመጣ ነው፡፡
የሻምበል ምህረት