አዲስ አበባ ዘንድሮ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን ታስተምራለች

You are currently viewing አዲስ አበባ ዘንድሮ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን ታስተምራለች

AMN – መስከረም 5/2019 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ በይፋ ተጀምሯል፡፡

ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች፣ መምህራንና የትምህርት ማህበረሰብ አባላትም በየትምህርት ቤታቸዉ በመገናኘት፤ ሰንደቅ አላማ በመስቀልና ችቦ በማብራት የመማር ማስተማር ሂደቱን መጀመር በይፋ አብስረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ለትምህርት ዘመኑ የሚያስፈልጉ የመማሪያ መጻሕፍት፣ ቁሳቁሶችና የመማሪያ ክፍሎች ዝግጅት አስቀድሞ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው የተማሪዎች ምገባ አገልግሎትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍም ትምህርት ከተጀመረበት እለት አንስቶ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2019 የትምህርት ዘመን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ለመማር መመዝገባቸዉንና አብዛኞቹ በትምህርት ገበታቸዉ ላይ መገኘታቸዉን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የወላጆችን የኢኮኖሚ ጫና የሚቀንሱ የመማሪያ ቁሳቁሶችን አስቀድሞ ያለምንም ክፍያ በነፃ ለተማሪዎች ተደራሽ ማድረጉ ለወላጆች ትልቅ እፎይታን እንደሰጠ ወላጆች ገልጸዋል።

‎የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል “በትምህርት ለትውልድ” መርሃ-ግብር እየተደረገ ባለዉ ጥረት ህብረተሰቡ፣ ባለሀብቶች እና አጋር ድርጅቶች የበኩላቸዉን ድርሻ በማበርከት ላይ የሚገኙ ሲሆን የተጀመሩት የድጋፍ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል፡፡

በመዲናዋ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ተማሪዎች በመልካም ስነ ምግባር ታንጸው ውጤታማ እንዲሆኑ፤ በሒሳብና በሳይንስ ፈጠራ ትምህርቶች የላቀ ዉጤት እንዲያስመዘግቡ ከወላጆችና ከሌሎች የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ነዉ የገለጹት፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር ለማሻሻል ባከናወናቸዉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን በ2019 የትምህርት ዘመንም ከአምናው የተሻለ ዉጤት ለማስመዝገብ አቅዶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review