የአዲስ አበባ የህብረብሔር ድምቀት እና የለውጥ መዲናነት ሚስጥር

AMN – መስከረም 5/2019 ዓ.ም

አዲስ አበባ የበርካታ ህብረብሔራዊ በዓላት መድመቂያ በመሆን የዓለምን ትኩረት ስባለች።

በመዲናዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተከናወኑ ሰፊ የኮሪደር ልማቶች ለባህላዊ ብዝሃነትና ለቱሪዝም እድገት ምቹ አካባቢን በመፍጠር፣ የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍ አድርገውታል።

እንደ መስቀል፣ ኢሬቻ፣ ጥምቀት፣ ሻደይ፣ አሻንዳ፣ ሶለን፣ ሸኖዬ እና ጎቤ እንዲሁም ሀገራዊ የድል መዘከሪያዎች ያሉ ታላላቅ የአደባባይ በዓላት የምትደምቅበት ገጽታዋ ዓለምን እየሳበ ይገኛል።

ከተማዋ የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች እሴቶችን ያቀፈች፣ ዓለም አቀፍ ትኩረት የምትስብና ጥልቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የተጎናጸፈች ከተማ ከሆነች ሰንብታለች።

ከተማዋ የጸጥታ መዋቅሯን በማጠናከር፣ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ ያመጣቻቸው ለውጦች ዜጎች ያለ ስጋት በአደባባይ ወጥተው በነጻነት በዓላቶቻቸውን እንዲከብሩ አስችሏቸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ የተከናወኑ ሰፊ የኮሪደር ልማቶች፣ የተስተካከሉ የከተማ መንገዶች፣ ውብ አደባባዮች እና ፓርኮች ለበዓላት መከወኛ የሚሆኑ ምቹ እና ማራኪ አካባቢዎችን ፈጥረዋል።

እነዚህ ውብ ስፍራዎች በዓላቱ በፎቶ እና በቪዲዮ ሲቀረጹ ውበታቸው ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ቱሪስቶች ከፍተኛ መስህብ አላቸው።

በተለይም እንደ ኢሬቻ፣ ሻደይ፣ አሻንዳ እና ሶለን የመሳሰሉ የሰፊ ሕዝብ በዓላት በአዲስ አበባ አደባባዮች መከበራቸው የከተማዋን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት እና የባህል ብዝሃነት እያረጋገጡ ይገኛሉ።

ይህ ደግሞ ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር በበዓላቱ ላይ የሚታየውን ሕዝባዊ ተሳትፎ በግንባር ቀደምትነት አነቃቅቷል።

መዲናዋ በዓላትን በድምቀት ማክበሯ እንደ ዲፕሎማሲያዊ ከተማ ብቻ ሳይሆን የቱሪዝም ማዕከል ያላት ስም ከፍ እንዲል አድርጓል።

በዓላትን ታኮው የሚመጡ እጅግ ብዙ የውጭ ቱሪስቶች እና ከክልሎች የሚመጡ እንግዶች የሆቴል፣ የትራንስፖርት እና የንግድ እንቅስቃሴውን በማነቃቃት የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍ አድርገውታል።

በአጠቃላይ አዲስ አበባ ዛሬ ላይ የቆመችበት የሰላም፣ የልማት እና የህብረብሔር ጥላ በዓላቷን ከባህላዊ ክዋኔ ባለፈ የሰላም እና የአብሮነት ማሳያ የድምቀት መድረክ አድርጓቸዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review