AMN – መስከረም 6/2019 ዓ.ም

ዴሞክራሲ ማህበረሰቦች በሰላም፣ በፍትህ እና በእኩልነት እንዲተዳደሩ ከሚያስችሉ አይነተኛ ስርዓቶች መካከል አንዱ ነው።
ዴሞክራሲ ለአንድ ሃገር ህዝብ ልማት እና እድገት በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብ፣ የማደራጀት እና የማመን መብቶች እንዲጠበቁ ዋስትና ይሰጣል።

በፀና የሀገረ-መንግስት እና የሀገር-ግንባታ ጉዞ ላይ የሚያጠነጥን ሰፊ ማዕቀፍም ነው ዴሞክራሲ፡፡
መሪዎች በህዝብ ምርጫ ብቻ እንዲሾሙ፣ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር፣ ስልጣናቸውንም በአግባቡ እንዲጠቀሙ፣ እኩልነት እንዲረጋገጥ ፣ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲስተናገዱ እና የተለያዩ ሃሳቦችና እምነቶች በውይይትና በምክክር እንዲፈቱ አስቻይ መድረኮችንም ይፈጥራል።
የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ ዴሞክራሲ ፍጹም የሆነ ስርዓት ባይሆንም፣ ዜጎች የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ባለቤት እንዲሆኑ እና መብቶቻቸው እንዲከበሩ የሚያስችል ከሁሉ የተሻለ አማራጭ ነው።

ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ አመታት የሃገሪቱን ህዝቦች ሁለንተናዊ ጥያቄዎችን የሚመልስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ጥረት ብታደርግም ሊሳካላት አልቻለም፡፡
ይልቁንም በወቅቱ የነበሩት መንግስታዊ ሥርዓቶች በተለይ የብሄር፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን ዴሞክራሲዊ ጥያቄ ወደ ጎን በመተው፤ ስልጣን ላይ ለመቆየት በመምረጣቸው የሰላም፣ የፍትህ የእኩልነት፣ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እና መሰል የመብት ጥያቄዎች ተጠናክረው እንዲነሱ ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ሃገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት በገባው ቃል መሰረት የብሄር ፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን፤ ሃይማኖቶችን እና ማንነቶችን ነጻነት እና እኩልነት የሚያረጋግጡ መሰረቶች ተጥለዋል፡፡
የጸና-ሃገረ መንግስት እና ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በጽኑ ተቋማት ላይ እንደመሆኑ መጠን መንግስት ለተቋማት ግንባታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

እስካሁን ድረስ በተሰሩት ስራዎችም ህዝቡን በሀገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ ከማድረግ፤ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ከማካሄድ፤ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን እውን ከማድረግ፤ ብሔራዊ መግባባትን ከመፍጠር እና የተቋማትን ቀጣይነት ከማጽናት ረገድ በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡

በመገንባት ላይ የሚገኘው ዴሞክራሲ ከመደመር እሳቤ የመነጨ የመግባባት ዴሞክራሲ በመሆኑ በአይነቱ የተለየ፤ አካታች እና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ነው።

በህዝባዊ ምርጫ ያሸነፈው ፓርቲ ሁሉንም ጠቅልሎ የሚወስድበት ሳይሆን፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃገረ መንግስት ግንባታ ሂደቱ ተሳታፊ የሚሆኑበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
እየተገነቡ ያሉት ተቋማት ከስርዓት እና ከግለሰቦች ለውጥ በላይ የሚጸኑ፤ ሀገርን እና ህዝብን የሚያገለግሉ፤ መንግስት ቢቀየር እንኳን የማይነቃነቁ እና ሀገርን የሚያጸኑ ተቋማት ናቸው፡፡
አሰባሳቢና ገዢ ትርክት በሃገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለው እንደመሆኑ መጠን ሂደቱ ፖለቲካዊ እና መዋቅራዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ጥልቅ የባህል እና የእሳቤ ግንባታ ሂደት ጭምር እንዲሆን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡
እየተገነቡ የሚገኙት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እና ተቋማት ሀገር እንድትጸና እና ትውልድ እንዲቀጥል የሚያደርጉ ብቻ ሳይሆኑ በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን መተማመን የሚያጠናክሩ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ያካሄደችው ሃገራዊ የምክክር ጉባዔም የመግባባት ዴሞክራሲ ዋንኛ መገለጫ ሲሆን፤ ሃገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያን ከማጽናት፣ ብሔራዊ መግባባትን ከማምጣት እና የጋራ ራዕይን በመፍጠር ረገድ ያለውን ሚና የላቀ ነው፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ