በአዲሱ የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገናል- መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች

AMN- መስከረም 6/2019 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ በትናንትናው እለት በይፋ ተጀምሯል።

በትምህርት ዘመኑ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸውንና አብዛኞቹ ተማሪዎች በመጀመሪያው የትምህርት ቀን በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘታቸውን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።

በአዲሱ የትምህርት ዘመን በከተማዋ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ስኬታማ የመማር ማስተማር ለማካሄድና የተማሪዎችን ውጤት ሊያሻሽሉ የሚችሉ ሰስራዎች መሰራታቸውን ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን፣ መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሰረት ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምቹ፣ ሳቢና ማራኪ እንዲሆኑ በማድረግ የመማር ፍላጎታቸውን የሚያነሳሱ የዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን የልደታ ካቶሊክ ካቴዲራል ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር በላይ አባተ ተናግረዋል።

የኤሎን አካዳሚ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ኤፍራታ ዮሐንስ በበኩላቸው፤ የተሟላ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር እና ተማሪዎችን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚያስችሉ አስፈላጊ ግብአቶች መሟላታቸውን አረጋግጠዋል።

መምህርት አመዘነች ፀጋ በበኩላቻ የነገ አገር ተረካቢ ሕፃናትን በትምህርትና በፍቅር ኮትኩቶ ለማሳደግ ለተሻለ ውጤት ለማብቃት በከፍተኛ ጉጉትና ደስታ ወደ ሥራቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ርዕሳነ መምህራኑና መምህራኑ አዲሱ የትምህርት ዘመን ለተማሪዎች አዲስ የእውቀት ጉዞ እንዲሁም ለመምህራን አዲስ የኃላፊነት ዘመን መሆኑ እንደሚገባው ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ባለፈው ዓመት የተመዘገበውን ስኬት በማስቀጠል ዘንድሮም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን አስታውቋል።

የትምህርት ሂደቱን ጥራትና ሰላማዊነት ለማረጋገጥ የትምህርት ቢሮ ማኔጅመንት ከየደረጃው አካላትጋር በመቀናጀት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎችን ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እያከናወነ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

በተለይም ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በተረጋጋ መንፈስ የሚማሩበት፣ መምህራንም በነፃነት የሚያስተምሩበት ሰላማዊ ቦታ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።

ይህ የተቀናጀ አሰራርና ዝግጅት በትምህርት ዘመኑ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብና የመማር ማስተማር ሂደቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ ተስፋ የጣለ መሆኑ የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review