የመደመር ዴሞክራሲ – የብዝሃነት ማማ ለሆነችው ኢትዮጵያ ፍቱን መፍትሔ

AMN – መስከረም 11/2019 ዓ.ም

በበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ቋንቋዎችና ሃይማኖቶች ባለጸጋነቷ የምትታወቀው ኢትዮጵያ፣ አንድ ብቸኛ ቡድን ብቻ አብላጫ ድምፅ አግኝቶ ብቻውን መጓዝ ፈተና በሆነበት በዚህ ዘመን ፍቱን መፍትሔው የመደመር ዴሞክራሲ ነው፡፡

የህግ እና የፌደራሊዝም ባለሙያው አቶ በላይ ወንዲሻ ከእጅ አዙር የውክልና ዴሞክራሲ እስከ የመግባባት ዴሞክራሲ ያለውን ታሪካዊ ጉዞ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል።

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ፣ የመደመር ዴሞክራሲ ጽንሰ-ሀሳብ በቁጥር ብዙም ሆነ ጥቂት የሆኑ ህዝቦች በሀገር ጉዳይ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው የሚያደርግ እና ለሰላም፣ ለልማት እንዲሁም ለጋራ ግንባታ ቁልፍ ሚና ያለው ተመጋጋቢ መርህ ነው።

ከቀጥታ ዴሞክራሲ ተነስቶ እስከ ውክልና፣ ህገ-መንግስታዊ እና የተግባቦት ዴሞክራሲ ደረጃዎች መሸጋገሩን ያነሱት አቶ በላይ፤ በተለይ ብዝሃነት ባለባቸውና አብላጫ ድምፅ ለማግኘት አስቸጋሪ በሆነባቸው ሀገራት የመግባባት ዴሞክራሲ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ቋንቋዎችና ሃይማኖቶች ባሉበት ሀገር አንድ ብቸኛ ቡድን አብላጫ ድምጽ ላያመጣ ይችላል።

በዚህ ጊዜ አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ መሄድ ስለማይቻል፣ ሁሉንም አካታች የሚያደርግ አሰራር ያስፈልጋል ነው ያሉት ባለሙያው።

የመደመር ፅንሰ-ሀሳብም ኢትዮጵያ ያሏትን ብዝሃነቶች አንድ ላይ በማጣጣም፣ በሀገር ጉዳይ ላይ ፍጹም የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል።

የመግባባት ዴሞክራሲ እና የመደመር ፅንሰ-ሀሳብ የሁሉንም ዜጎች መብትና ሚዛን የሚጠብቁ፣ እጅግ ተመጋጋቢ መርሆዎችን የያዙ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

አቶ በላይ አክለውም ይህ አሰራር ለሀገር እድገት፣ ለሰላም እና ለዴሞክራሲ ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመደማመጥ እና በመምክር የሚዳብረው የዴሞክራሲ ተሳትፎ ውጤታማ እንዲሆን፣ እንደ ሀገር የተጀመሩ መነጋገሮችና ምክክሮች ለሀገራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠትን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review