AMN መስከረም 13/2019 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሃገር መከላከያ ሠራዊት ሥነ ልቦና ጥንካሬ እና ሁለንተናዊ ብቃት የሚመነጨዉ ከጽኑ የሃገር እና የህዝብ ፍቅር ነዉ።
ሠራዊቱ በሃገሩ ህልዉናና ሉዓላዊነት ላይ ከማንም ጋር የማይደራደር ጠንካራና ክንደ ብርቱ ሲሆን የተሠጠዉን ግዳጅ በጽናትና በቁርጠኝነት መፈጸም የሚችል ነዉ፡፡
የቀኑ ሃሩር ፣ የሌሊት ቁር ፣ ዳገቱና ቁልቁለቱ የማይበግረዉ ጀግናዉ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ለሃገሩና ለወገኑ ክብር በጽናት የሚታገል የጀግንነት መገለጫም ነዉ።
አለም ከደረሰበት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር እኩል ለመራመድ ራዕይ ሰንቆ በመስራት ላይ የሚገኘዉ ሠራዊቱ የተሠጠዉን ግዳጅ በአስተማማኝ መልኩ በአጭር ጊዜ ዉስጥ መፈጸም የሚያስችለዉን ዐቅምና ቁመናም በመገንባት ላይ ይገኛል።
የአየር ኃይልን ጨምሮ የተለያዩ የሠራዊቱ ክፍሎች አሁን ላይ የታጠቋቸዉ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ከሃገሪቱ አልፎ የቀጣናዉን ሠላምና ደህንነት በብቃት ማረጋገጥ የሚችሉ ናቸዉ።
ሰራዊቱ ከሃገር ዉጭ በተለያዩ የሰላም ማስከበር ስራዎች ላይ በመሰማራት የተሰጠዉን ግዳጅ በብቃት መፈጸሙም የሰራዊቱን ዐቅምና ቁመና የሚገልጽ ነዉ፡፡
የሃገር መከላከያ ሰራዊት የአሸናፊነቱ ሚስጥር የህዝብ ድጋፍና አብሮነት ያለዉ መሆኑ ሲሆን የሃገሪቱ ህዝቦችም ለጀግናዉ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ትልቅ ከበሬታ አላቸዉ፡

የህዝብ ፍቅር ከታጠቀው ዘመናዊ መሳሪያና ቴክኖሎጂ በላይ የተገነባበት ሥነ ልቦናና የሚተማመንበት አቅሙ ነው።
በዚህ ህዝባዊና ሃገራዊ ፍቅር በተለያዩ ጊዜአት የጠላት እኩይ አላማን ከማክሸፉም በላይ የሃገር ሉዓላዊነትን አስከብሮ ጠንካራ ሃገረ መንግስት እንዲፈጠር አስችሏል፡፡
ከህዝብ አብራክ የተገኘና በዋናነት ሃገር የመጠበቅ አላማን አንግቦ የተሰለፈዉ ይህ ሰራዊት፤ ጠላት የሚያሰራጨው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሊለውጠው ፣ የፈጠራ ትርክት ሊያደበዝዘው ፣ የነበርና የይሆናል ትንበያ ሊያዛባው የማይችል ጽኑ ሰራዊት ነዉ፡፡
ሰራዊቱ እንደትናንትናዉ ሁሉ ዛሬም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት ላይ የሚቃጡ ማንኛዉንም ትንኮሳዎች በአጭር ጊዜ ዉስጥ መመከት በሚያስችል አቋም ላይ መገኘቱም ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ ትልቅ ኩራት ነዉ፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ