AMN – መስከረም 13/2019 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቅጠል ተራ 960 ቤቶች በአራት ወር ውስጥ ገነብተን ከቦታው ላይ ለተነሱ ነዋሪዎች አስተላልፈናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፣ ቅጠል ተራ ለመኖር እጅግ ምቹ ያልነበረ ፤ ለሰው ልጅ ክብር የማይመጥን ፤ እጅግ የቆሸሸ ፣ የተፋፈገ እና የተጨናነቀ በመሆኑ የሰው ህይወትም በአስከፊ ሁኔታ በእሳት አደጋ ያጣንበት አካባቢ ነበር ብለዋል።
ዛሬ ግን እጅግ ያማሩ ፥ ዘመናዊና ሁሉንም ነገር የተሟሉላቸው ባለ 9 ወለል የሆኑ ብዛታቸው 9 ህንጻዎች ተገንብተው ወደ ምቹ መኖሪያ አካባቢ ተቀይሯል ሲሉ ገልጸዋል።
“የመርካቶ የበጎነት የመኖሪያ መንደር” በ11, 000 ካሬ ሜትር ላይ የተገነቡ G+8 የሆኑ ዘጠኝ (9 )ብሎኮች ሲሆኑ ( ባለ ሁለት መኝታ 112፣ ባለ አንድ መኝታ 336 እና ስቱዲዮ 112 በድምሩ 560 የመኖሪያ ቤቶች) እና ሰፊ የስራ እድልን የሚፈጥሩ 371 የንግድ ሱቆች በአጠቃላይ 960 ቤቶች ያሉት መሆኑን ከንቲባ አዳች ዘርዝረዋል፡፡
በውስጡም የህጻናት የመጫወቻ ስፍራ፣ የስፓርት ማዘውተሪያ( የኳስ ሜዳ፣ ቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስ፥ የሰውነት ማጎልመሻ ቦታዎች) ፥ ለነዋሪዎች የመኪና ማቆምያ ፓርኪንግ፥ ለኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ፥ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ፥ዘጠኙም ብሎኮች ላይ የጋራ መጠቀሚያ ሰገነት፥ ሊፍት፥ የፍሳሽና የኤሌክትሪክ መስመሮች በዘመናዊ መልክ ተሟልተው መገንባታቸውንም ጠቅሰዋል።

ይህ በመርካቶ የበጎነት የመኖሪያ መንደር የሰው ህይወትን የሚቀይር ፥ መርካቶ አካባቢን “ተራ” በሚል ስያሜ የተሰጣቸው ( ቅጠል ተራ፣ ጭድ ተራ፣ ገብስ ተራ፣ ሳር ተራ፣ ቦንብ ተራ … ወዘተ) ጎስቋላ አካባቢዎችን ወደ ውብ አካባቢ የመለወጥ ጉልህ ማሳያ ነው ብለዋል።
ቃል በተግባር ማለት ይህ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፥ እንደዚህ ዓይነት የተወሳሰበ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ለሰው ልጆች የሚመጥኑ ፥ ነዋሪዎች የክብር ኑሮ እንዲኖሩ፥ ህይወታቸውን የሚቀይሩ ተግባራትን ያለ እረፍት 24/7 በመፈፀም ነዋሪዎች አዲስ ህይወት እንዲጀምሩ ማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል ።
የስራዎቻችንን ማዕከል ሁሉ ሰው ተኮር አድርገን፥ ከተማችን ውብ ፅዱ፥ ለነዋሪዎቻችን የተመቸች ከተማ እንድትሆን ያለ እረፍት የመስራት ተግባራችን ይበልጥ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ካላችሁ አካፍላችሁ ከከተማ አስተዳደራችን ጎን በመሆን የበጎ ተግባር ላይ የተሰማራችሁ፥ ዛሬም በቅጠል ተራ የበጎነት መንደር እንድንቀይር ያገዛችሁን በተለይ ፕሮፌሰር ሰናይት ፍስሃ፥ በግንባታው የተሳተፋችሁ ሁሉ በነዋሪዎች ስም ከልብ እናመሰግናለን ሲሉም ገልጸዋል።
ቅጠል ተራ ወደ “መርካቶ የበጎነት መንደር “ ተቀይፘል ሲሉም በመልዕክታቸውን ገልጸዋል፡፡