አላግባብ የተወሰደውን የማስመለስ ሕጋዊ ጥያቄ – የባህር በር

AMN- መስከረም 17/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የትናንት ስህተትን የማረም ወሳኝ እርምጃ ላይ ትገኛለች፡፡

ቀደም ሲል የሀገሪቱን ስልጣን ተቆጣጥረው የነበሩ አካላት የሕዝቦቿን የኢኮኖሚ ዕድገትና ጂኦፖሊቲካዊ ሚዛን የሚወስኑ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞቿን አሳልፈው በመስጠታቸው ዘላቂ ህልውናዋ አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ እንድትሆን ይሁንታ በመስጠት ፣ ማንኛውም ሀገር ወዳድ ህዝብ በግልጽ ያየውንና የተረዳውን ስትራቴጂካዊ ስጋት በወቅቱ የነበሩት ሹማምንት ማየት አለመቻላቸው ኢትዮጵያን ለትልቅ የኢኮኖሚ ኪሳራና ለደህንነት ስጋት ዳርጓታል።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትለይ ያኔ የነበረው አስተዳደር ወዲያውኑ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ድርድር ለኤርትራ ዕውቅና ሲሰጥ የኢትዮጵያ ወሳኝ የባሕር በር ጉዳይ ተነሥቶ ውይይት አልተደረገም ፤ የሕዝቧም ጥቅሞች እንዴት እንደሚጠበቁ አልተደራደሩም።

በወቅቱ ስልጣን የተቆናጠጠው አካል የኢትዮጵያን የባህር በር ያለምንም ሕጋዊ አካሄድ አሳልፎ በመስጠት የታሪክ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ ውሳኔው ታላቅ የታሪክና የፖሊሲ ስህተት ነበር፡፡ ይህን ስህተት ለማረም ነው መንግሥት ዐቢይ አጀንዳ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችው የባሕር በር ይገባኛል ጥያቄም አላግባብ የተዘጋውን በር የማስከፈትና ሀገራዊ ጥቅምን የማስከበር ሕጋዊ ርምጃ ነው።

የኢትዮጵያ ጥያቄ የዓለም አቀፋዊ ሕጋዊ ድጋፍ ያለው ነው፡፡ የቪየና ስምምነትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የባሕር ሕጎች መሠረት ኢትዮጵያ ወደ ባሕር የመድረስና የመጠቀም መብት አላት።

ኢትዮጵያ የባሕር በር መልሳ እንድታገኝ ታሪክም ይደግፋታል፡፡ የኢትዮጵያ በታሪክ የቀይ ባህርን ስታስተዳድር የቆየች እንደመሆኗ አላግባብ በግዴለሽነት የተወሰደባትን ይህን የባሕር በር መልሳ ልታገኝ ይገባል፡፡

ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የወደፊት ህልውና እና የኢኮኖሚ ዋስትና ሊረጋገጥ የሚችለው ከወደብ ጥገኝነት የተላቀቀ እንደሆነ ብቻ ነው።

ጥያቄው የኢኮኖሚ ጫና ከመቀነስ ባሻገር የነገዋን ኢትዮጵያ መሠረት የማጽናትና የትናንት ተበዳይቷን የመካስ አሻጋሪ እንቅስቃሴ ነው፡፡

ትናንት የተሠሩትን የፖሊሲና የስትራቴጂ ስሕተቶች በማረም ፣ የታሪክና የሕግ ማስረጃዎችን በማመዛዘን የሚገባትን የጠየቀችው ኢትዮጵያ አላግባብ የተዘጋባትን በር በማስከፈት ፍትህ ማግኘቷም ጥርጥር የለውም፡፡

ዓለም አቀፉ ማሕረሰብ የኢትዮጵያ ያነሳቸውን ጥያቄ ተገቢነቱን በመቀበል ድጋፋቸውን ያሳዩ ሲሆን ፣ ጎረቤት ሀገራትም የኢትዮጵያን ጥያቄ በአዎንታዊ ተርድተው ፣ ለቀጠናዊ ትስስር ፣ አብሮ የመልማት እና የጋራ ደህንነት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review