AMN – መስከረም 24/2019 ዓ.ም
የፌደራል መንግሥት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ጨምሮ ሰላምን ለማስፈን ሲሰራ የቆየ ቢሆንም፣ የህወሓት ቡድን ግን ስምምነቱን ለጊዜ መግዣነት፣ ሠራዊት ለማሰልጠን እና ትጥቅ ለማሰባሰብ ሲጠቀምበት መቆየቱን አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ።
ህገወጡ የህወሃት ቡድን ትግራይን ለፖለቲካ ቁማሩ መጠቀሚያ አድርጎት ቆይቷል ያሉት ዶ/ር አብርሃም፤ ቡድኑ የተፈናቃዮችን አጀንዳ ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ በማድረግ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ እንቅፋት ሆኖ እንደቆየም ገልፀዋል።
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡት (ዶ/ር) አብርሃም፤ የፌደራል መንግሥት የተከተለው የሰላም ፍላጎትና ብስለት የተሞላበት አመራር የቡድኑን እውነተኛ ገጽታ ለህዝብ ግልጥልጥ አድርጎ ማሳየቱን ተናግረዋል።
ከግጭቱ አስቀድሞም ሆነ በሂደቱ የህወሓት ቡድን በዲያስፖራውና በዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ላይ የውሸት ትርክት በመገንባት እውነታውን ለመሸፈን ሲንቀሳቀስ መቆየቱንም ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ መንግሥት የትግራይ ሕዝብ በራሱ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲተዳደር እድል በመስጠቱ እና መንግሥት ምንም ዓይነት ልዩ አጀንዳ እንደሌለው በተግባር በማሳየቱ፣ ማህበረሰቡ የቡድኑን የዘረፋና የጥፋት ፍላጎት በራሱ ተግባር ተረድቶ ጀርባ ሰጥቶታል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን በትርምስ ውስጥ ለማቆየት የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ከሻዕቢያ ጋር በመቀናጀት የውስጥ ባንዳዎች የከፈቱት ጥቃት በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እየተቀለበሰ ይገኛል።
የኢትዮጵያ የጸጥታ ተቋማት ባላቸው ከፍተኛ ወታደራዊ ዲሲፕሊንና ዝግጁነት የጥፋት ኃይሎችን ተልዕኮ እያመከኑት መሆኑንም (ዶ/ር) አብርሃም ገልፀዋል፡፡
አሁን ላይ የትግራይ ዋና ከተማ መቐለ በፌደራሉና በአጋር ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መግባቷን ተከትሎ፣ የመከላከያ ሰራዊት አካባቢውን የማጽዳት ሥራ እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የትግራይ ህዝብ ራሱ በራሱ የሚያስተዳድርበትን ሥርዓት ለመዘርጋትም የአስተዳደር መዋቅሮች በህዝብ ተሳትፎ እንዲደራጁ እየተደረገ ሲሆን፣ ተፈናቃዮችም በሰላም ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው።
በቀጣይ ወራት ውስጥ ክልላዊ ምርጫ በፍጥነት ለማካሄድ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን (ዶ/ር) አብርሃም ተናግረዋል።
በበረከት ጌታቸው