በኅብረ-ብሄራዊ አንድነት ጽኑ መሠረት ላይ የሚመሠረተዉ አዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት

AMN – መስከረም 25/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች ባህሎችና ማንነቶች መገኛ ነች፡፡

የብዝሃነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ መላው ህዝቦቿ በመከባበር፤ በመቻቻልና በእኩልነት የሚኖሩባት የነፃነት ምድርም ነች፡፡

በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩል ድርሻና ተሳትፎ ያላቸው ህዝቦቿ፤ ዛሬ ላይ ታፍራና ተከብራ የኖረችውን ኢትዮጵያ በመገንባት ሂደት ውስጥ የላብና የደም ዋጋ ከፍለዋል፡፡

በሀገራቸው ሉዓላዊነትንና ኅልውና ከማንም ጋር የማይደራደሩት ኢትዮጵያውያን፤ ጠላት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመድፈር በሞከረባቸው ጊዜያት ሁሉ በጋራ ዘምተው፤ በጋራ ተዋግተው፤ በጋራ ድል አድርገዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በተለያዩ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ የሚቆሙት ህዝቦቿ፤ በህገ-ወጥ መንገድ ያጡትን የባህር በር ለማስመለስም በኅብረት ቆመዋል፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ ጋር በተያያዘ በምክር ቤትም ሆነ በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ የሚገባቸውን ውክልና፤ እውቅናና ክብር ያገኙት የኢትዮጵያ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በልማቱም መስክ በጋራ ሰርተው፤ በጋራ የሚያድጉበት ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡

ከለውጡ ወዲህ በሃገሪቱ የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች፤ ሃይማኖቶች፤ ቋንቋዎች፤ ባህሎችና ማንነቶች የሚገባቸውን ህገ-መንግሥታዊ መብት በመጎናጸፋቸው ፤ ዛሬ ላይ የብሄር ብሄረሰቦችና ማንነቶች መብት ከመከበሩም በላይ ማንኛውም ዜጋ የፈለገውን ሃይማኖት የመከተል፤ በፈለታ ቋንቋ የመማር፤ የመናገርና የመተዳደር፤ ባህሉን የማሳደግ ሙሉ መብት አግኝቷል፡፡

ከአሁን ቀደም የልዩነትና የክፍፍል መንስኤ የነበረው ጨፍላቂ፤ አግላይ እና አክራሪ አመለካከት በኅብረ-ብሄራዊ አንድነት፤ በወንድማማችነትና በአብሮነት እሴት በመተካቱ ዜጎች በሃገራቸው ላይ በብሄራቸው፤ በሃይማኖታቸው፤ በቋንቋቸው፤ በባህላቸውና በማንነታቸው ምክንያት ሳይሸማቀቁ፤ በእኩልነት የመኖር መብት አግኝተዋል፡፡

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የራስን ብቻ ሳይሆን የሌላውን ብሄር፤ ሃይማኖት፤ ባህል፤ ቋንቋና ማንነት አክብሮ መኖር የዘመናዊነት እና የሥልጣኔ ምልክት እየሆነ ከምጣቱም በላይ የሌላውን ብሄር፤ ሃይማኖት፤ ባህል፤ ቋንቋና ማንነት መንካት የህግ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡

ከነጠላና ሃሰተኛ ትርክቶች የሚመነጩ፤ የህዝቦችን አብሮ መኖር ሲፈትኑና ለአደጋ ሲያጋልጡ የነበሩ ጽንፈኛ፤ ዘረኛ፤ አክራሪና በጥላቻ የተሞሉ እሳቤዎችም በእኩልነት፤ በወንድማማችነትና በአብሮነት እሳቤዎች እየተተኩ መምጣታቸውም በኢትዮጵያ የጋራ ትርክትን ለመገንባት ትልቅ መሰረት ጥሏል፡፡

ሁሉም ዜጎች በሀገቸው ላይ እኩል ህገ-መንግስታዊ መብት ማግኘታቸው፤ ብዝሃነት እና ኅብረ-ብሄራዊ አንድት እየተጠናከረ መምጣቱ መላው የሃገሪቱ ዜጎች በእኩልነትና በአንድነት መንፈስ ለሀገራቸው ልማት፤ ሰላምና እድገት በጋራ እንዲቆሙ፤ ብሎም ታላቋን ኢትዮጵያ በጋራ እንዲገነቡ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡

ህብረ- ብሄራዊ አንድነት ታላቋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ትክክለኛዉ መሠረት ሲሆን አዲስ የሚመሰረተዉ መንግስትም በወንድማማችነትና በእኩልነት ላይ በተመሠረተዉ በዚህ ጽኑ መሠረት ላይ ቆሞ የኢትዮጵያን ብልጽግና እዉን ለማድረግ ይሠራል።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review