ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባስመዘገበቻቸው ውጤቶች የአፍሪካን የማስፈጸም አቅም እያሳየች ነው – ዶ/ር መቅደስ ዳባ

You are currently viewing ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባስመዘገበቻቸው ውጤቶች የአፍሪካን የማስፈጸም አቅም እያሳየች ነው – ዶ/ር መቅደስ ዳባ

AMN – ህዳር 16/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባስመዘገበቻቸው ተጨባጭ ውጤቶች የአፍሪካን የመቻል አቅም በተግባር እያሳየች መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡

5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን፤ ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ታዳሚዎች በጉባኤው እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት፤ ከጤናው ዘርፍ ባሻገር የገንዘብ፣ የዕቅድ፣ የግብርና እና የአካባቢ ጥበቃ ዘርፎችን የወከሉ ከ46 በላይ ሚኒስትሮች በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል፡፡

የጉባኤው ታዳሚዎች የኢትዮጵያን ውጤታማ ተሞክሮዎች እንዲሁም ከጤናው ዘርፍ ባለፈ በሌሎች መስኮች እያስመዘገበች ያለችውን ሁለንተናዊ ለውጦች ተመልክተዋል።

ይህም ሀገሪቱ ያላትን የመሥራትና የመፈጸም አቅም በተግባር በማሳየት፣ በአህጉሪቱ ላይ እምነት እንዲጣል ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን አብራርተዋል።

መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የአጋር ድርጅቶችና የግል ዘርፍ ተወካዮች በጋራ እየተወያዩበት ባለው በዚህ መድረክ፤ ኢትዮጵያ በሳይንሱ ዘርፍ ያከናወነቻቸውን አበይት ሥራዎች በተለያየ መንገድ እያቀረበች ትገኛለች ብለዋል።

በተጨማሪም ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል ጤና፣ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ እና በሕክምና ሪፈራል ሥርዓት ዘርፍ ያከናወነቻቸውን ውጤታማ ሥራዎች መመልከታቸውን አስረድተዋል።

በተለይም የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች የማኅበረሰቡን ጤና በዲጂታል መንገድ የሚከታተሉበትን የኤሌክትሮኒክ የማኅበረሰብ ጤና መረጃ ሥርዓት በተግባር ማየት መቻላቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በርካታ ሀገራት የኢትዮጵያን ሞዴሎችና የዲጂታል አሠራሮች በሀገራቸው ለመተግበር ፍላጎት በማሳየታቸው የልምድ ልውውጥ እየተደረገ ይገኛል።

የዓለም የጤና አስተዳደር ሥርዓት እየተቀየረ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር መቅደስ፤ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንድትሆን ኢትዮጵያ የጤና ዲፕሎማሲን በስፋት እየተጠቀመችበት ትገኛለች ብለዋል።

ጉባኤው የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነት ወደ ተጨባጭ ውሳኔዎች የሚያሸጋግር መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ አፍሪካ በዓለም አቀፍ የጤና ውይይቶችና በሳይንስ ትግበራዎች ተቀባይ ብቻ ሳትሆን ሰጪም ሆና እየወጣች መሆኗን አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በተከታታይ የተካሄዱት ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ጉባኤዎች ለዚህ መድረክ ስኬት መሠረት መሆናቸውንም አክለው መግለፃቸውን ኤዚአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review