AMN – ህዳር 17/2019
የአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ መንግስት የሱዳን ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት ለማካሄድ ላቀረበው የሰላም አማራጭ እውቅና ሰጠ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ሁሉም የሱዳን ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ውይይት መድረክ እንዲመጡ ይፋዊ የሠላም ጥሪ ማቅረቧን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሱዳናውያን በራሳቸው ፍላጎት ዘላቂ ሰላም የሚያመጡበትን ሁሉን አቀፍ የውይይት መድረክ ለማስተናገድና ለማመቻቸት ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ ዓሊ ዩሱፍ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሱዳን ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት ያቀረበውን የሰላም ሀሳብ በአጽንኦት መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ሊቀመንበሩ፣ የሱዳን ባለሥልጣናት በዚህ ሀሳብ ዙሪያ የሰጡትን ምላሽና የያዙትን አቋም በቅርበት መከታተላቸውን ገልጸዋል።
በመግለጫቸውም፣ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ይህ የውይይት ሀሳብ በሱዳን ተፋላሚና ባለድርሻ አካላት መካከል ምክክር እንዲጀመርና እንዲዳብር የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው እና ህብረቱም እውቅና እንደሚሰጠው አመልክተዋል።
የአፍሪካ ህብረት በሱዳን የተከሰተውን ግጭት በህብረቱ መመስረቻ ቻርተር እና አግባብነት ባላቸው የህብረቱ ሕጎች መሠረት፣ በውይይትና በድርድር ብቻ አካታችና ሰላማዊ እልባት እንዲያገኝ የማይናወጥ ቁርጠኝነት አለው ነው ያሉት።
የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የብሩንዲ ፕሬዝዳንት ኤቫሪስቴ ንዳዪሺሚዬ በሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት፣ ኮሚሽኑ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመተባበር ለመደገፍ ሙሉ ቁርጠኝነት እንዳለው ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል።