የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ ባለብዙ ዘርፍ መፍትሔዎችን በመተግበር ላይ ይገኛል

You are currently viewing የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ ባለብዙ ዘርፍ መፍትሔዎችን በመተግበር ላይ ይገኛል

AMN – ኅዳር 18/2019 ዓ.ም

ከተማ አስተዳደሩ ከተለመደው አሠራር በመውጣት ጊዜን፣ ወጪንና ጉልበትን የሚቆጥቡ አማራጭ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት እየተጠቀመ ነው።

የመኖሪያ ቤት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታትም ከመንግሥት በጀት በተጨማሪ በመንግሥትና በግል አጋርነት፣ በቤት ልማት ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ በሪል እስቴት አልሚዎችና በበጎ ፈቃደኞች አማካኝነት በርካታ ቤቶችን በተለያዩ አካባቢዎች እየገነባ ይገኛል።

በተለይም በመልሶ ማልማትና በኮሪደር ልማት ምክንያት ለሚነሱ ነዋሪዎች እንዲሁም ለዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ በመስጠት፣ ቤቶቹ በፍጥነት ተገንብተው ለተጠቃሚዎች እንዲተላለፉ እየተሠራ ነው።

ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ 496 ሺህ 971 ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች እፎይታን ያጎናፀፉ ሲሆን፣ በተጨማሪም መንግስት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በአምስት ዓመታት ውስጥ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት በተያዘው ሀገራዊ ዕቅድ መሠረት፣ በአዲስ አበባ በ21 ሳይቶች የ100 ሺህ ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነና አብዛኞቹም በመጠናቀቅ ላይ ናቸው።

በግንባታ ሂደቱ ረጃጅም ሕንፃዎችን በአጭር ጊዜ መገንባት የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ሲሆን፣ ቤቶችን በፍጥነት የሚያመርቱ ፋብሪካዎችም ሙከራ ጀምረዋል። ፋብሪካዎቹን ወደ ሙሉ ሥራ ለማስገባት የግብአት ማስተካከያዎች እየተደረጉ ይገኛሉ።

እነዚህ የቤት ልማቶች ንጹሕ የመኖሪያ አካባቢ ከመፍጠራቸው በተጨማሪ የልጆች መጫወቻ፣ የእግረኛ መንገዶችና የማኅበራዊ ግንኙነት ማጠናከሪያ ስፍራዎች የተሟሉላቸው፣ የዜጎችን ክብር የሚመጥኑ መኖሪያ መንደሮች መሆናቸውንም ከአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልማት ተነሺዎችን፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን፣ አረጋውያንን፣ የሀገር ባለውለታዎችንና ሌሎች ቤት ፈላጊዎችን የቤት ባለቤት በማድረግ፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያካተተ የልማት ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review