አዲስ አበባን የአፍሪካ የሕክምና ማዕከል ለማድረግ መሰረት ተጥሏል

You are currently viewing አዲስ አበባን የአፍሪካ የሕክምና ማዕከል ለማድረግ መሰረት ተጥሏል

AMN- ኅዳር 16/2019 ዓ.ም

በባህላዊ ህክምና የተጀመረው የዓለማችን የጤና እና ህክምና አገልግሎት ዛሬ ላይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ወደሚታገዝበት ደረጃ ደርሷል።

እንደ ኤክስ-ሬይ፣ ሲቲ ስካን እና ኤምአርአይ ያሉ ቴክኖሎጂዎች የውስጥ አካላትን ሳይቀዱ በግልጽ በማየት ትክክለኛ ምርመራ ለማድረግ አስችለዋል።

በሮቦት የታገዙ ቀዶ ህክምናዎችም ህመምን በመቀነስ ታካሚዎች በፍጥነት እንዲያገግሙ አድርገዋል።

በርካታ የዓለም ሀገራት የኩላሊት፣ የልብ እና የጉበት ንቅለ ተከላዎችን በስኬት በማከናወን ለብዙዎች ተጨማሪ የመኖር እድል ሰጥተዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያም በሽታን ቀድሞ ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ዘመኑ የደረሰበትን የህክምና ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ የላቀ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት እየሰራች ትገኛለች፡፡

በተለይ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ፣ ከነዋሪቿ አልፎ በከተማዋ ለሚኖሩ የውጭ ሀገራት ዜጎች የላቀ የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚችሉ የጤና ተቋማትን እየገነባች ነው፡፡

ለተለያዩ ህክምናዎች ወደ ውጪ ሀገራት የሚሄዱ ግለሰቦች በሀገራቸው ላይ የተሻለ ህክምና ማግኘት የሚችሉበትን አቅምም እየፈጠረች ነው፡፡

አዳዲስ ዘመናዊ ሆስፒታሎችን በመገንባት፣ ነባር ሆስፒታሎችን በማደስና ተጨማሪ አገግሎቶችን እንዲሰጡ በማድረግ በዘርፉ ከፍተኛ እመርታን አሳይታለች፡፡

የአበበች ጎበና እናቶችና ህጻናት ሆስፒታል፣ ላፍቶ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ኮልፌ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና የገላን ድንገተኛ ህክምና ሆስፒታል በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተገነቡ የህክምና ማዕከላቶች ናቸው።

በዳግማዊ ሚኒሊክ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል፣ በዘውዲቱ እና በራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢ ሆስፒታልም የማስፋፊያና የተጨማሪ ማዕከላት ግንባታ ተከናውኗል፡፡

ዘጠኝ አዳዲስ የጤና ጣቢያዎች ተገንብተው ወደ አገልግሎት የገቡ ሲሆን፣ ከአርባ የሚበልጡ ጤና ጣቢያዎች ደግሞ መሰረታዊ ማስፋፊያ ተደርጎላቸዋል፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት የነበሩት የአልጋዎች ቁጥር ሁለት እጥፍ ያደረገ ሲሆን፣ የጤናና የህክምና አገልግሎቶችም ከሰው ንክኪ የጸዱ ዲጂታላይዝድ ተደርገዋል፡፡

ከመንግስት በተጨማሪ በርካታ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን የሕክምናውን ዘርፍ በመቀላቀል ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ይህም መዲናዋ ተመራጭ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን የሰነቀችውን ራዕይ እየደገፈ ይገኛል፡፡

አሁን ላይ በሀገሪቱ በኤም አር አይ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) የሚሰሩ የዲጂታል ኤክስሬይ፣ የካንሰር እና የልብ ሕክምና፣ ዘመናዊ የላብራቶሪ አገልግሎቶች፣ የኦክስጅን ማምረቻዎች ወደ አገልግሎት ገብተዋል፡፡

የፎሬንሲክ ኬሚስትሪ እና የስነ ምረዛ ዲ ኤን ኤ ምርመራ፣ የኩላሊት እጥበት እና የፎረንሲክ አገልግሎት በሀገሪቱ ከሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የልብ፣ የኩላሊት ንቅለ ተከላ፣ የካንሰር ሕክምና እና የአጥንት ቀዶ ህክምናዎች መሰጠት መጀመራቸውም ለሕክምና ወደ ውጭ የሚደረግ ፍልሰትን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶታል።

የሕክምና ልህቀት ማዕከላትን የማልማት ጅማሮዎቹ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ይበልጥ እያሳደገ ይገኛል፡፡

በቀጣይ ዓመታትም የሕክምና ቪዛ አሰጣጥን በማቀላጠፍና የጤና መድኅን ሥርዓቶችን ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ማስተሳሰር አዲስ አበባን የአፍሪካ የሕክምና ማዕከል ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

የመደመር መንግሥት ከህክምናው በተጨማሪ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review