AMN – ጥቅምት 3/2019 ዓ.ም

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢፌዴሪ መንግሥት እና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል ለኃይል ሴክተር ሪፎርም ኢንቨስትመንትና ማዘመኛ ምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ145.8 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።

7ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ፍቃዱ ተሰማ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ የብድሩ ዓላማ የአዲስ አበባን የኃይል ማስተላለፊያ መረብ ለማጠናከር፣ አዳዲስ የኃይል ጣቢያዎችን መገንባትና ነባሮቹን ማሻሻል እንዲሁም የመሬት ውስጥ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን መዘርጋት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለምታስተናግደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP 32) አስተማማኝና ዘመናዊ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ የብድር ስምምነቱ ሚናው የጎላ መሆኑን ሚኒትሩ ተናግረዋል።

ብድሩ ቀላልና አነስተኛ የገንዘብ ጫና የሚፈጥር ተብሎ የተገለጸ ሲሆን የ6 ዓመት የእፎይታ ጊዜን ጨምሮ በ 31 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑንም ተብራርቷል።
የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ አያይዘውም ብድሩ ከሀገሪቱ የብድር አሰጣጥና አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣምና ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ምክር ቤቱ የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅጁን አዋጅ ቁጥር 1441/2019 አድርጎ በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።