AMN- ጥቅምት 3/2019 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማውን አጠናቀቀ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ እንዳሳሰቡት፣ በቀጣይ የሚከናወኑ ሥራዎች በቁጥር ብቻ ሳይሆን ለህዝቡ በሰጡት አገልግሎት እና ባስገኙት ትርጉም ያለው ውጤት ይመዘናሉ ብለዋል።
አብዛኛዎቹ ሴክተሮች የሠሯቸውን ሥራዎች ውጤት አካተው ሪፖርት ቢያደርጉም፣ አንዳንዶች ግን የሥራውን ብዛት (ቁጥር) ብቻ እንደ ውጤት አድርገው አቅርበዋል።
ይህ አሰራር በቀጣይ የሚቀየር በመሆኑ፣ ሥራዎች ለህዝቡ ምን ጥቅም እንደሰጡ እና ምን ያክል ሰዎች በአገልግሎቱ እንደተጠቀሙ በሚያሳይ አዲስ የውጤት መለኪያ ሥርዓት ይመራሉ።
በሚቀጥሉት ሶስት ወራት በየደረጃው ያሉ አካላት ዝርዝር ግብ ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል ያሉት ከንቲባዋ፣ በዚህም፣ማን ምን ያህል እንደሚሠራ፣ሥራው መቼ እና እንዴት እንደሚከናወን፣አስፈላጊዎቹ ግብዓቶች ምን እንደሆኑ በግልጽ ይቀመጣሉ ብለዋል።
በተጨማሪም ሥራዎች ሳይሠሩ ሲቀሩ እና ክፍተት ሲፈጠር ምክንያቱ በግልጽ ይለያል።
ለክፍተቱ ተጠያቂው አካል ማን እንደሆነ፣ ተጠያቂነቱ መረጋገጡን እና የተሰጠውን መፍትሄ የሚያሳይ ዝርዝር ዕቅድ ይኖራል።
ሁሉም አካላት በአንድ ዓይነት ደረጃ (ስታንዳርድ) እንዲመሩ የድጋፍ ሰነዶች በየደረጃው ይሰራጫሉ።
በቀጣይ 90 ቀናት የተለዩ የትኩረት መስኮችን መነሻ በማድረግ ሁላችንም ሥራዎቻችንን በአግባቡ ቆጥረንና አቅደን መፈጸም እንደሚገባን አሳስበዋል።
በየሻምበል ምህረት