AMN – ጥቅምት 4/2019 ዓ.ም

ከረጅም ዓመታት በፊት ሀገራቸውን ለቀው በጀርመን ሀገር ኑሮአቸውን መስርተው ከቆዩት ወገኖች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ስዩም ሙልጌታ፣ ከ45 ዓመታት በኋላ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ በመመለስ በአዲስ አበባ ከተማ የታዘቧቸውን የልማት ለውጦች አጋርተዋል።

አቶ ስዩም ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ ቀደም ሲል በነበረውና አሁን ባለው የከተማዋ ገጽታ መካከል ሰፊ እና አስደናቂ ልዩነት እንዳለ መመልከታቸውን አንስተዋል።
አቶ ስዩም፣ ከተማዋን ሲያስታውሷት ያኔ በጣም አነስተኛ እንደነበረች ጠቅሰው፣ አሁን ላይ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ ግዙፍ እና አስደናቂ ዕድገት ማሳየቷን ተናግረዋል።
በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመሠረተ ልማት፣ በመንገዶች መስፋፋት እና በፓርኮች ግንባታ የተከናወኑ ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ እንደቀየሩት ገልጸዋል።
ለዚህም ማሳያ ያደረጉት አራዳ ፓርክ የሚገኝበትን አካባቢ ሲያስታውሱ፤ ከዚህ ቀደም አካባቢው የንጽህና ዕጦት የነበረበት፣ የወንዝ ሽታ የሚረብሽበት እና ሰዎች በምቾት መንቀሳቀስ የማይችሉበት ሁኔታ እንደነበር ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ግን አካባቢው ሙሉ በሙሉ ተለወጦ ንጹህና ማራኪ መሆኑን በምስክርነት ያቀረቡ ሲሆን፣ በተጨማሪም የትራፊክ ፍሰትን በተመለከተ ቀደም ሲል የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ በማስታወስ፣ አሁን ላይ የእግረኛና የመኪና መንገዶች በግልጽ ተለይተው በመሰራታቸው እንቅስቃሴዎች የተሳለጡና ደህንነታቸው የተጠበቁ መሆናቸውን አድንቀዋል።
አቶ ስዩም፣ በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የተቋማት ግንባታዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ይሁን እንጂ አሰራሮች ስር እስኪሰዱ እና ህብረተሰቡ ሙሉ በሙሉ እስኪለማመዳቸው ድረስ የተወሰነ ጊዜ እንደሚወስድ አብራርተዋል።
በተለይም በሀገሪቱ የጌጣጌጥ፣ የወርቅ እና የብረት ስራ ሙያዎችን በዘመናዊ መልኩ በማስተማር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለገበያ ማቅረብ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሀገር ውስጥ ምርቶች የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲወጡና የቱሪስቶችን ትኩረት እንዲስቡ ከተፈለገ፣ ከባህላዊ አሰራር ወጥቶ በሰለጠነ የቴክኒክ እውቀትና በዲዛይን ጥንቃቄ መደገፍ እንዳለበት አሳስበዋል።
አቶ ስዩም እና አጋራቸው ከወር በኋላ እንደገና ወደ ሀገራቸው በመመለስ፣ በወርቅ ስራ እና በባህላዊ የዕጅ ባለሙያ ዘርፍ ላይ ያተኮሩ የአጭር ጊዜ ስልጠናዎችን እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
ይህ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ከሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ጋር ተቀናጅቶ ሲሰራ፣ የኢትዮጵያን የዕጅ ጥበብ ውጤቶች ዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ ለማድረስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተስፋ ተጥሎበታል።
በወርቅነህ አቢዮ