AMN – ጥቅምት 4/2019 ዓ.ም

የማንኛውም ህብረተሰብ መሻት በሰላም ወጥቶ መግባት ፣ ሰርቶ መለወጥና የመሠረታዊ አገልግሎቶችን በአግባቡ ማግኘት ነው።
በትግራይ ክልል በሕገወጡ የህወሃት ቡድን የጥፋት እንቅስቃሴ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ እንደ ባንክ፣ ቴሌኮም እና የአየር ትራንስፖርት ያሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች የፌዴራል መንግሥት በወሰደው ቁርጠኛ እርምጃ በፍጥነት ወደ ሥራ መግባታቸው የሕዝቡን የቆየ የሰላምና የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ፍላጎት የመለሰ ሆኗል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቀሌ የሚያደርጋቸውን መደበኛ በረራዎች እንደገና ማስጀመሩ ሕዝቡ በነጻነት እንዲንቀሳቀስ ያስቻለ ሲሆን ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በክልሉ የሚገኙ ቅርንጫፎቹን ክፍት በማድረግ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ በሕብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ እፎይታን ፈጥሯል።

እነዚህ አዎንታዊ እርምጃዎች የክልሉን ሕዝብ ወደ ሰላማዊ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ እየመለሱት ይገኛሉ።
ከቀናት በፊት በዓዲ ጉዶም ከተማ የተካሄደው ደማቅ ሕዝባዊ ሰልፍ የትግራይ ክልል ህዝብ ፍላጎትና አቋም በግልጽ የተንጸባረቀበት ነው፡፡
ሕዝቡ ወደ አደባባይ በመውጣት ለፌዴራል መንግሥት የሰላም ጥረቶችና አገልግሎቶችን የመመለስ እርምጃዎች ያለውን ሙሉ ድጋፍ ገልጿል።
ሰልፈኞቹ የተገኘው ሰላም የመንግሥት የፈጣን ምላሽ ውጤት መሆኑን ገልጸው መንግሥት ይህንን ሰላም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ይህም የትግራይ ሕዝብ ለረጅም ዓመታት ሲደርስበት የነበረውን አፈናና ጭቆና አውልቆ በመጣል፣ የተገኘው ሰላም እንዲጠናከርና የመልሶ ማቋቋሙ ሥራ እንዲፋጠን ያለውን ፍላጎት በግልጽ ያመላክታል።

የሕዝቡ የሰላም ፍላጎት በሰልፎች ብቻ ሳይገደብ የልጆቹን ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስን በመደገፍ ጭምር አረጋግጧል።
በክልሉ ተቋርጦ የቆየው የትጥቅ ማስፈታትና የታጠቁ ኃይሎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስን ያካተተው የዲ.ዲ.አር ሂደት እንደገና መጀመሩ ለዘላቂ ሰላም መንገድ እየጠረገ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከግጭት ወጥተው ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ የመረጡ ታጣቂዎች የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ማዕከላትና ወደ ፌዴራል መንግሥት የተሃድሶ ማዕከላት እየገቡ እንደሚገኙ ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት።
ቀደም ሲል ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን የፕሪቶሪያውን ስምምነት በማፍረስ ታጣቂዎች ወደ ተሃድሶ ማዕከላት እንዳይገቡ ሲያደናቅፍ ቢቆይም ፣ የሕዝቡ የሰላም ፍላጎትና የመንግሥት ቁርጠኝነት አሸንፏል።
ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያው እንደገለጹት ፣ በአሁኑ ወቅት ከ63 ሺህ በላይ የትግራይ ታጣቂዎች የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ተሃድሶ ማዕከላት ገብተዋል፡፡
ይህም የትግራይ ሕዝብ ከግጭት ይልቅ የልጆቹን ሰላማዊ ተሃድሶና እድገት መምረጡን የሚያሳይ ሲሆን ፣ ለረጅም ዓመታት ከነበረበት ጭቆናና አፈና ተላቅቆ ወደ አዲስ የሰላምና የልማት መስመር መሸጋገር መጀመሩንም ያመላክታል።
የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ሕይወት እየገቡ ያሉ ወገኖች ለክልሉ መልሶ ማቋቋምና ለሀገር ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁነታቸውን እያሳዩም ይገኛሉ፡፡
የትግራይ ሕዝብ ፍላጎቱን በግልጽ አሳውቋል ፤ እሱም ሰላም ፣ ልማት፣ የመሠረታዊ አገልግሎቶች መስፋፋት እና የልጆቹ ወደ ሰላማዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት መመለስ ነው።
መንግሥት ለሕዝቡ የሰላምና የልማት ጥያቄዎች የሰጠው ፈጣን ምላሽና የሕዝቡ አጋርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ አዎንታዊ ውጤቶችን ለማስመዝገብ አስችሏል።
ወደፊትም የተገኘውን ሰላም በማጠናከር፣ የሀገርን ሉዓላዊነት የመጠበቅና የብልጽግና ጉዞዋን አጠናክሮ የመቀጠል እቅድ እንዲሳካ የሕዝቡ ንቁ ተሳትፎና የጽናት ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
በታደሰ ሽፈራው