AMN ጥቅምት 4/2019

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ አዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ ያስተናገደችውን የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች አመራር ኢኒሼቲቭ (AMALI) የ2026 የአመራሮች ፎረም ተሳታፊዎችን ተቀብለናል ብለዋል፡፡

ይህ መድረክ ልምድ ለመለዋወጥ፣ እርስ በርስ ለመማማርና ከተማችን እያካሄደች ያለውን የለውጥ ጉዞ ለማካፈል ጠቃሚ ዕድል ፈጥሯል።
የከተማችን የለውጥ ጉዞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አርቆ አሳቢነትና ለከተማዋ ባስቀመጡት ራዕይ የተቃኘ ነው ብለዋል፡፡
ይህንን ራዕይ ወደ ተጨባጭ የልማት ውጤቶች እየቀየርን ነው። በትራንስፖርት፣ በቤቶች ልማት፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አገልግሎቶችና በትውልድ ግንባታ ላይ በምናከናውናቸው ሥራዎች የነዋሪዎቻችንን ተጠቃሚነት እያረጋገጥን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በራሳችን የፋይናንስና የዕውቀት አቅም ላይ ተመሥርተን በመሥራታችን፣ የአዲስ አበባ ተሞክሮ ለሌሎች የአፍሪካና የዓለም ከተሞች ጠቃሚ ትምህርቶችን እያበረከተና አዳዲስ የልማት ዕድሎችን እያመላከተ መሆኑ ያስደስተናል።

በተለይም አዲስ አበባን በአፍሪካ ህፃናትን ለማሳደግ ምርጥ ከተማ ለማድረግ ያለንን ጽኑ ቁርጠኝነት እያሳየን ነው። በሕፃናት እድገት (ECD) ላይ ያተኮሩ ተግባራትን በማጠናከር፣ የሕፃናትን ደህንነት፣ ትምህርትና የወደፊት ሕይወት በከተማችን የልማት አጀንዳ ማዕከል ላይ አስቀምጠናል ብለዋል፡፡
ከየአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች አመራር ኢኒሼቲቭ (AMALI) መሪዎችና የፎረሙ ተሳታፊዎች ጋር በመሆን፣ በከተማችን በልዩ ሁኔታ የተገነባውንና ለፕሮግራሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባደረገችው ክብርት ሊዛ ዲዬጎ መታሰቢያ የተሰየመውን የሕፃናት እንክብካቤ ማዕከል መርቀን ለአገልግሎት ከፍተናል፡፡
ለዚህ መርሐ ግብር ስኬት አስተዋጽኦ ያደረጉትን የቢግ ዊን ፊላንትሮፒ መሥራች፣ ሊቀመንበርና ፕሬዝዳንት ጄሚ ኩፐርን፣ የፋውንዴሽኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ከሠተ አድማሱን፣ አማካሪዎችንና የፕሮግራሙን አመራሮች በሙሉ ከልብ አመሰግናለሁ ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡