AMN – ጥቅምት 5/2019 ዓ.ም

የአንድ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ጥንካሬና ብቃት የሚለካዉ በቁጥር ብቻ ሳይሆን በገነባዉ ሥነ ልቦና፤ በታጠቃቸዉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂያዎች እና ሌሎች ታክቲካዊ መስፈርቶች ጭምር መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ሃገራዊ ለዉጡን ተከትሎ ኢትዮጵያ እየገነባች የምትገኘዉ የመከላከያ ሃይልም እነዚህንና ሌሎች ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን በማሟላት ላይ የሚገኝ ነዉ፡፡
የሰራዊቱ የስልጠና እና የችሎታ ደረጃ፣ የውጊያ ብቃት፣ የአመራር ክህሎት፣ የዲሲፕሊን ደረጃ እና በፍጥነት ምላሽ የመስጠት ዝግጁነት ከመቼዉም ጊዜ በላይ ተጠናክሯል፡፡
ሰራዊቱ የጦር መሳሪያዎችና የቴክኖሎጂ የበላይነት ያለዉ ሲሆን በአየር ኃይል፣ በምድር ኃይል፣ በባህር ኃይል፣ በሳይበርና በኤሌክትሮኒክስ ውጊያ ከቅርብ አመታት ወዲህ የተገነባዉ አቅምም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነዉ፡፡

ኢትዮጵያ ዘመናዊ የጦር አዉሮፕላንና ጄቶችን፣ የውጊያ ድሮኖችን፣ የመጓጓዣና የጥቃት ሄሊኮፕተሮችን ብዛት እና በጥራት እየገነባች ነዉ፡፡
በምድር ኃይል፣ በባህር ኃይል፣ በሳይበርና በኤሌክትሮኒክስ ውጊያ ዉስጥ ያሉ ሌሎች አቅሞችም እንዲሁ ዘመኑን የሚመጥኑና የሰራዊቱን የመፈጸም አቅም የሚያልቁ ናቸዉ፡፡
የሰራዊቱን የመፈጸም አቅም ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ በጥናትና ምርምር ዘርፍ በርካታ አኩሪ ስራዎች በመሰራት ላይ የሚገኙ ሲሆኑ፤ ሰራዊቱ ከአህጉር እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ላይ የገነባችዉ የመከላከያ ሰራዊት በየትኛዉም ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ በአየር ሁኔታ፣ በቆዳ ስፋት፣ በተፈጥሮ ሁኔታዎች የማይበገርና ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ እናት ሃገሩን መጠበቅና ሉዓላዊነቷን ማስከበር የሚችል ነዉ፡፡
ሰራዊቱን ልዩ የሚያደርገዉ ዋንኛ መስፈርት ከአድዋ ጀግኖች የወረሰዉ ጠንካራ የማሸነፍ መንፈስ፣ የሃገር እና የወገን ፍቅር፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነቱ እና የስነ ልቦና ብቃቱ ነዉ፡፡
ሰራዊቱ ጠንካራ ህዝባዊ ድጋፍ ያለዉ ሲሆን፣ ከሰላማዊ ሁኔታዎች በተጨማሪ የተለያዩ ግዳጆች በሚኖሩበት ወቅት ህዝቡ ደጀን ሆኖ ከአጠገቡ ይሰለፋል፤ ያበረታታዋል፤ ይደግፋዋል፡፡
በሃገር ዉስጥም ይሁን ከሃገር ዉጪ የተለያዩ የሰላም ማስከበር ግዳጆች በሚኖሩበት ወቅትም ህዝቡ ለሰራዊቱ ደማቅ የጀግና አቀባበል ያደርግለታል፤ አለኝታነቱን እና ጋሻዉ መሆኑን ይገልጸለታል፡፡
ሰራዊቱ በበኩሉ ከሚሰጡት ግዳጆች ጎን ለጎን የተለየዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን በመስራት፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስና በመገንባት፣ የደረሱ እህሎችን በማሰባሰብ፣ ደም በመለገስ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ወገኖቹን በመደርዳት የህዝብ ልጅ መሆኑን ያስመሰክራል፡፡
ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ የምትገኘዉ ሰራዊት እነዚህንና መሰል ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟላ፣ በጠላቶቹ የሚፈራ፣ በወገኖቹ ዘንድ የሚወደድና ትልቅ ክብር ያለዉ ነዉ፡፡
ሰራዊቱ የሃገሪቱን ሉዓላዊነት በጀግንነት ከማስከበር አልፎ በቀጣናዉ ለሚፈጠሩ የጸጥታ ስጋቶች አስተማማኝ እና ጠንካራ ሰራዊት መሆኑም በበርካቶች ዘንድ እየተመሰከረለት ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተለያዩ የሰላም ማስከበር ስራዎች ላይ ያለዉ ክብርና ዝና እንዲሁም የሰዉ ልጆችን ያለምንም አድልዎ በሰብዓዊነት በማገልገሉም ትልቁ የሰራዊቱ መታወቂያዉ ሆኗል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ