የህገ-ወጡ ህወሓት ቡድን ውድቀት ለትግራይ ህዝብ የፈጠረው እፎይታ

You are currently viewing የህገ-ወጡ ህወሓት ቡድን ውድቀት ለትግራይ ህዝብ የፈጠረው እፎይታ

AMN – ጥቅምት 9/2019 ዓ.ም

በትግራይ ሕዝብ ላይ ለዓመታት ሰቆቃና መከራ ሲያስከትል የቆየው ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን፣ በሰላም ወዳዱ የትግራይ ሕዝብ ቁርጠኝነትና በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ በመጨረሻም ከሀገሪቱ የፖለቲካና የህዝብ ጫንቃ ላይ ሙሉ በሙሉ መወገዱ ተረጋግጧል።

ቡድኑ በግብፅና በሻዕቢያ ቀጥተኛ ድጋፍ በመታገዝ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እና ለመበታተን ያነገበውን እኩይ ዓላማ ለማሳካት ለ4ኛ ጊዜ ከፍተኛ የጦርነት ድግስ አሰናድቶ የነበረ ቢሆንም፣ በጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በትግራይ የሰላም ሰራዊትና በሰላም ወዳዱ ህዝብ የተቀናጀ ተጋድሎ ላይመለስ ተደምስሷል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ፈጣንና ታሪካዊ ግስጋሴ የቡድኑ አባላት የጦር መሳሪያቸውን እየጣሉ መፈርጠጣቸው፣ ለትግራይ ሕዝብና ለመላው ኢትዮጵያውያን አዲስ የሰላም፣ የነጻነትና የእፎይታ ምዕራፍ የከፈተ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።

ይህ ህገ-ወጥ ስብስብ ላለፉት አሥርት ዓመታት በትግራይ ሕዝብ ላይ እንደ መዥገር በመጣበቅ፣ ክልሉን ከልማትና ከዕድገት ወደኋላ በማስቀረት ለከፍተኛ ችግር እና ለከፋ ቀውስ ዳርጎት ቆይቷል።

በተለይም በቅርቡ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች አጀንዳ በመሸከም፣ ከግብፅ መንግስት የተደረገለትን የዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችና የፋይናንስ ድጋፍ በመቀበል ኢትዮጵያን ለማተራመስና ውድቀቷን ለማፋጠን ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱ ተመላክቷል።

ሆኖም የቡድኑ እኩይ አካሄድና በሕዝብ ስም የሚያራምደውን የጥፋት አላማ፣ የትግራይ ህዝብ ባሳየው ጽናት የተሞላበት ቁርጠኝነትና በመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት፣ ህገ-ወጥ ቡድኑ በደረሰበት ሽንፈት፣ የክልሉ ሕዝብ ከጭቆና እና አፈና ነጻ ወጥቶ የነጻነት አየር መተንፈስ ጀምሯል።

የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የትግራይ የሰላም ሰራዊት እና ሌሎች የጸጥታ አካላት በከፈሉት ከፍተኛ መስዋዕትነት በየግንባሩ አስደናቂ የድል ብስራቶችን አስመዝግበዋል።

ሰራዊቱ የህገ-ወጡን ቡድን ምሽጎችና የጥፋት መዋቅሮች በመደምሰስ፣ የክልሉን ሕዝብ ከጽንፈኛው ስብስብ ከበባ በማላቀቅና የሕግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ከፍተኛ የጀግንነት ገድል ፈጽሟል።

ይህ የተመዘገበው ድል የጸጥታ ማስከበር ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት የእውነተኛ ሕዝብና የሀገር ጋሻ መሆኑን ዳግም ያረጋገጠበት ነው።

ሰራዊቱ ባሳየው የላቀ ወታደራዊ ስነ-ምግባርና ህዝባዊ ፍቅር የተሞላበት ጀብድ፣ ህገ-ወጡ ቡድን በውጭ ኃይሎች ታግዞ ሲነዛው የቆየውን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሙሉ በሙሉ በማፈራረስ የሕዝቡን አመኔታ ማትረፍ ችሏል።

የፌዴራል መንግስት ለትግራይ ሕዝብ ያለውን ጥልቅ ወገንተኝነትና አጋርነት በተግባር ለማሳየት፣ ክልሉ ከቡድኑ ነጻ መውጣትን ተከተሎ ሰፊ የሰብአዊ እርዳታ የማቅረብና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ማፋጠን የጀመረ ሲሆን፣ በርካታ የእህልና የመድኃኒት እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በስፋት እየገቡ ይገኛሉ።

ከእርዳታ እህል ማከፋፈል ጎን ለጎን፣ ህገ-ወጡ ቡድን በፈጠረው እክል ምክንያት የተቋረጡ እንደ መብራት፣ ስልክ፣ ባንክና የንጹህ መጠጥ ውሃ ያሉ መሠረታዊ የአገልግሎት መስመሮችን የመጠገንና በፍጥነት ወደ ሥራ የማስገባት ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ይህ የመንግስት ፈጣን ምላሽ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

ከህገ-ወጡ ቡድን ነጻ የወጣው የትግራይ ክልል፣ አሁን ላይ እንደ ማንኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች በሰላምና በልማት የመበልጸግ ሰፊ ዕድልና ተስፋ ከፊቱ ይጠብቀዋል።

የክልሉ ሕዝብ ከፌዴራል መንግስትና ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በተባበረ ክንድ በመቀናጀት፣ የቀደመውን ታሪካዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ወደ ታላቅ የብልፅግና ጉዞ የሚሸጋገርበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

በአጠቃላይ፣ የህገ-ወጡ ህወሓትና የውጭ ደጋፊዎቹ እቅድ መክሸፍ ለትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት አዲስ ብርሃን የፈነጠቀ ነው።

የትግራይ ሕዝብ ከዚህ በኋላ በጦርነትና በሰቆቃ ሳይሆን፣ በልማት፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ ዕድገትና በጋራ ብልፅግና የሚታወቅበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንደሚሆንለት ይጠበቃል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review