AMN – ጥቅምት 10/2019 ዓ.ም
ቀይ ባህር የአንድ ወይም የጥቂት ሀገራት የግል ንብረት ሳይሆን ዓለም አቀፍ ንግድን የሚያገለግል የጋራ የውኃ መስመር ነው።
ከዚህ አኳያ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በአለም አቀፍ ሕግ መሠረት የባህር በር የማግኘት ሕጋዊ መብት አላቸው።
ይህ መብት እ.ኤ.አ. በ1982 በወጣው የተባበሩት መንግስታት የባህር ሕግ ኮንቬንሽን አንቀጽ 112 ተደንግጎ የሚገኝ ሲሆን፤ የባህር በር አልባ ሀገራት ከባህር ለመድረስ እና ለመመለስ የባህር ዳርቻ ባላቸው ሀገራት ግዛት የመተላለፍ መብት እንዳላቸው በግልጽ ተደንግጓል።
ከ30 ዓመታት በፊት የባህር በርዋን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ያጣችው ኢትዮጵያ፣ በዓለም ትልቋ የባህር በር አልባ ሀገር እንደ መሆኗ መጠን የባህር በር ጥያቄዋ የህልውና፣ የሉዓላዊነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ የባህር በር የመጠቀም ፍላጎት የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነት በኃይል በመጣስ ሳይሆን፣ በድርድር፣ በሰላማዊ ውይይት እና በጋራ ጥቅም ላይ በመመሥረት ነው።
ይህ አቀራረብ የቀጣናውን ሰላም የሚያረጋግጥ እና የንግድ ትብብርን የሚያጠናክር በመሆኑ፣ የሁሉንም ትኩረት ይፈልጋል።
ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የውጭ ንግዷን በባህር የምታከናውን በመሆኗ፣ አስተማማኝ እና ሰላማዊ የባህር በር ማግኘት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለወደፊት ብሩህ ተስፋዋ ወሳኝ ነው።

የበለጸጉ ታላላቅ ሀገራት የንግድ እና ወታደራዊ ጥቅሞቻቸውን ማዕከል ባደረጉበት በዚህ ቀጠና፣ ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የንግድ መከወኛ የውኃ በር የማግኘት መብቷ እንዲረጋገጥ ጉዳዩ የሕዝብ አጀንዳ እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።
ሆኖም ይህ ጥያቄ ከጎረቤት ሀገራት ሉዓላዊነት ጋር እንዳይጋጭ በሰላም፣ በንግድ እና በጋራ ተጠቃሚነት በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት የቅንጦት ሳይሆን የሕዝቧን የልማትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መብት ለማረጋገጥ የሚደረግ ሕጋዊ ጥረት ነው።
ሀገሪቱ የጎረቤት ሀገራትን ሉዓላዊነት ሙሉ በሙሉ እያከበረች፣ በዓለም አቀፍ ሕግ የተረጋገጠውን የባህር በር መዳረሻ እና የቀጣናዊ ትብብር መብቷን ለማሳካት ጥረቷን ቀጥላለች።
በበረከት ጌታቸው