AMN – ጥቅምት 10/2019 ዓ.ም
የትግራይ ሕዝብ ፣ የታጠቁ ወጣቶች እንዲሁም የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላም እንዲመለሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በትግሪኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች እንደ ሕዝብ ወደ ሰላም መመለስ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
እናቶች ከልጆቻቸው ጋር ይገናኙ ፣ በብዙ ስቃይ ውስጥ ያለው የተጎዳው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ይነቃቃ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በምርጫ መደበኛ አስተዳደር እስኪመሰረት ድረስ ሕዝቡ አንድነቱንና ተቋማቱን መጠበቅ እንዳለበት የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከጸጥታ አካላት ጋር በተባባሪነት እንዲሰራም አሳስበዋል።
የታጠቁ ወጣቶች ትጥቃቸውን አስረክበው በሰላም እጃቸውን በመስጠት ወደ ዲ.ዲ.አር ሥርዓት እንዲገቡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ የፖለቲካና ወታደራዊ መሪዎችም በሰላም እጃችሁን ስጡ ፣ ይበቃናል፣ ሰላም ይሻላል ሲሉ አሳስበዋል።
ወንጀል የሠራ ሰው ካለ በሕግ እንደሚዳኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፣ ንጹህ ከሆናችሁ ደግሞ በሀገራችሁ በሰላም ኑሩ ፣ ስደት በስተርጅና በዛ ላይ ሀብታችሁን ጥላችሁ ወደ ኋላ ቀሮቹ መመለስ አያዋጣም የሚል ምክር አስተላልፈዋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ ትኩረቱን ወደ ሰላም፣ መሪዎቹን ወደ መምረጥ፣ ወደ መስኖና እርሻ ልማት፣ ወደ ማዕድን፣ ኢንዱስትሪና የከተሞች ኮሪደር ልማት እንዲመልስ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ፣ መንግሥትም ከሕዝቡ ጎን በመሆን ለመልሶ ግንባታና ለሰላም በትጋት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በታደሰ ሽፈራው