AMN – ጥቅምት 10/2019 ዓ.ም
የዘንድሮ 1448ኛው ዓመተ ሂጅራ የሀጅ ጉዞ ምዝገባ ጥቅምት 12 ጀምሮ እስከ ጥር 10/2019 እንደሚከናወን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።
ጠቅላይ ምክር ቤቱ የ1448ኛው አመተ ሂጅራ የሃጅ ጉዞ ምዝገባ ማስጀመሪያን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በዚህም ”የላቀ አገልግሎት ለሐጃጅ እርካታ” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባዘጋጃቸው የምዝገባ ማዕከላት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል።
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጁ 33 የሃጅ ምዝገባ ማስተባበሪያ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን የጠቅላይ ም/ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ኡስታዝ ተምኪን አብዱላሂ ተናግረዋል።
የልዩ መስተንግዶ (VIP) እና የትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሀጅ መስተንግዶ ምዝገባን በተመለከተ በቀጣይ ማብራሪያ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
ለሃጅ ጉዞ ለመመዝገብ የሚመጣ ማንኛውም ተጓዥ የጤና ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማቅረብ አስገዳጅ መደረጉን ገልፀው ምዝገባው በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ብቻ ይከናወናል ብለዋል።
ጠቅላይ ምክር ቤቱ የዘንድሮው የሀጅ ምዝገባ በተጠቀሰው ቀናቶች የሀጅ ተጓዦች እንዲመዘገቡም ጥሪ አቅርቧል።
በመሀመድኑር ዓሊ