AMN- ጥቅምት 10/2019 ዓ.ም
የአንድ ሀገር ጽኑ መሠረትና የህልውናዋ ዋስትና ጠባቂ የሆነው መከላከያ ሠራዊቷ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሰላም እና ሉዓላዊነት አስከብሮ ማቆየት ላይ ታሪካዊ ኃላፊነት የተሸከመ ታላቅ ተቋም ነው።
ይሁን እንጂ የዚህ ታላቅ ሠራዊት የትናንት ጉዞ ከፈተናዎች እና ከከባድ ተቋማዊ ስብራቶች ጋር የተያያዘ ነበር።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ፤ ተቋሙ የነበረበት ሁኔታ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ክብደት ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም፣ ከባድ የሎጀስቲክስና የመዋቅር ቀውስ ውስጥ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የተቋሙ መዋቅር እና አሠራር ከዘመናዊ የጦር ሳይንስና ከሠራዊት ግንባታ መርሆች የራቀ እና የሀገሪቱን ታላቅነት በበቂ ሁኔታ የማያንጸባርቅ ነበር።
የጦር መሣሪያዎችና የሎጂስቲክስ መጋዘኖቹ ያረጁ፣ የጥገና አቅሙም የደከመ እና የሠራዊቱ አባላት የሰፈሩባቸው ካምፖችና መሠረተ ልማቶች ለሰዎች ኑሮ ፈጽሞ የማይመቹ ነበሩ።
በወቅቱ የነበረው ተቋም “ኢትዮጵያን የማይመስል” የሚለው መግለጫ የቁመናውን ውድቀት፣ የሎጀስቲክስ እጥረቱን እና የመዋቅሩን መላላት በትክክል የሚያሳይ ነበር።
ሠራዊቱ የሀገርን ዳር ድንበር በጀግንነት ለመጠበቅ ቢያስብም፣ የሚመራበት ሥርዓትና የታጠቀው ትጥቅ ከዘመኑ ፍላጎት ጋር እጅግ የራቀ መሆኑም ሌላኛው ስብራት ነው።

ይህንን ለመቀልበስና የኢትዮጵያን ሕልውና ዘላቂ ዋስትና ለማረጋገጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የወሰዷቸው የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች የለውጡ መሠረት ሆነዋል።
ተቋማዊ ማሻሻያው በዋናነት ያነጣጠረው መከላከያን ከፓርቲና ከቡድን ጥቅም ነጻ በማውጣት፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍትሃዊ ውክልና የሚያረጋግጥ ብሔራዊ ሠራዊት አድርጎ እንደገና ለማዋቀር ነበር።
በዚህም ሠራዊቱ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ብቻ የሚጠብቅ፣ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ እና በሙያዊ ሥነ-ምግባር የተገነባ እንዲሆን አዲስ መዋቅር ተዘረጋ።
ሀገሪቱ በገባችባቸው ውስብስብ የደኅንነት ፈተናዎች ውስጥ ሆኖም፣ መከላከያን በዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች፣ በድሮን ቴክኖሎጂ፣ በአየር ኃይል ማጠናከሪያዎች እና በሰለጠነ የሰው ኃይል የማብቃት ሥራ ተሠራ።
ዛሬ ላይ ሠራዊቱ ከቀድሞው ድህነት ወጥቶ በሎጂስቲክስ አቅሙ፣ በስንቅና ትጥቅ ዝግጁነቱ የቀጣናውን ኃይል ሚዛን የሚመጥን ቁመና ይዟል። በዚህም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጀግንነት፣ የዲሲፕሊን እና የዘመናዊነት ምልክት ሆኗል።
በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በተከናወኑ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሠላም እና ሉዓላዊነት ለመድፈር የተነሱ አጥፊ ኃይሎችን በመደምሰስ ረገድ ያሳየው አፈጻጸም የለውጡን ትክክለኛነት በተግባር አረጋግጧል።
ሠራዊቱ የሕዝብ ልጅ በመሆኑ ከሕዝብ ጋር ያለውን ትስስር አጠናክሮ፣ በችግር ጊዜ ደራሽ፣ በሰላም ጊዜ የልማት አጋር በመሆን የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲስ ምዕራፍ እየጻፈ ይገኛል።
ትናንት ኢትዮጵያን የማይመስለው ተቋም ዛሬ ላይ የሀገሪቱ የክብር መገለጫ፣ የዜጎች ኩራት እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ ጽኑ ዓምድ ሆኖ ቆሟል።
በታምራት ቢሻው