ህወሃት ቅንጣት ታክል የትግራዋይነት ባህሪ የለውም-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

You are currently viewing ህወሃት ቅንጣት ታክል የትግራዋይነት ባህሪ የለውም-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

AMN – ጥቅምት 9/2019 ዓ.ም

የፖለቲካ ድርጅትን ደህንነት ከሕዝብ ህልውናና ደህንነት ጋር ማያያዝ መሠረት የሌለው የተሳሳተና አደገኛ አስተሳሰብ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር በትግሪኛ ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልከተው በሰጡት ማብራሪያ፣ የፖለቲካ ድርጅትን ደህንነት ከሕዝብ ህልውና ጋር ማያያዝ የሕዝብን ህልውና አደጋ ውስጥ ስለሚጥል አደገኛ ሀሳብ ነው ብለዋል።

ህወሓት ወደ አምሳ ዓመታት ገደማ ያስቆጠረ ድርጅት መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የትግራይ ሕዝብ ግን ለሺህዎች ዓመታት የነበረና ለወደፊቱም ለብዙ ሺህ ዓመታት የሚኖር ሕዝብ መሆኑን አስረድተዋል።

ህወሓት ከአምሳ ዓመታት በፊት እንዳልነበረና አሁንም ታሪክ እየሆነ መሆኑን በመጥቀስ፣ ከእሱ በፊት የነበሩት የኢትዮጵያ መሪዎች የተለየ እንዳልሆነና ከትግራይ ወጥቶ ኢትዮጵያን መምራት አዲስ ነገር እንዳልሆነ ገልጸዋል።

በዚህም አጼ ዮሐንስን ለአብነት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከትግራይ ወጥተው ሀገር መምራታቸውንና ዛሬ ባይኖሩም የትግራይ ሕዝብ ግን እንዳለ አብራርተዋል።

ህወሓት እየደበዘዘና እየከሰመ ቢሆንም ሕዝብ ግን እንደሚቀጥል፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች እንደሚመጡና እንደሚወድቁ፣ መንግስታትም እንደሚቀያየሩ ሕዝብና ሀገር ግን እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል።

የድርጅቱን ማንነት በተመለከተም ህወሓት እድሜው ማጠሩ ብቻ ሳይሆን፣ በቆይታውም ተመርምሮ ሲታይ የትግራዋይነት ጠረን እንዳልነበረው ጠቅሰዋል።

ድርጅቱ በትግራይ የበቀለ፣ አባላቱም አብዛኞቹ ተጋሩ መሆናቸው ቢታወቅም፣ ቅንጣት ታክል የትግራዋይነት ባህሪ እንደሌለው ገልጸዋል።

የመረጠው አስተሳሰብ፣ ወዳጅነቱ፣ የሚከተለው ፖሊሲና እምነቱ በቃላት እንጂ በተግባር የማይታይ በመሆኑ ከትግራይ ሕዝብ ክብር ጋር የሚመጣጠን ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።

የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ምክንያት ብዙ ዋጋ መክፈሉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፣ አሁን እውነታው ግልጽ እየሆነ መምጣቱ ደስ እንደሚያሰኛቸውና የትግራይ ሕዝብ እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ራሱን ችሎ እንደሚቀጥል፣ ሀገሩንም በመገንባት ረገድ እንደ ወትሮው የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review