AMN – ጥቅምት 9/2019 ዓ.ም
ህወሓት ትግራይን እንደ ግል ኩባንያው ተቆጣጥሮ የመግዛት አካሄድ ከእንግዲህ ሊደገም እንደማይገባና የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገውን የፖለቲካ አማራጭ የሚያንጸባርቅበትና የሚመርጥበት ነፃነት ሊረጋገጥለት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግሪኛ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት፣ ህወሓት ስልጣኑን ለማደላደል ሲል የትግራይን ሕዝብ በየአካባቢው ራያ፣ አጋሜ ፣ እንደርታ እያለ ሲከፋፍለው ቆይቷል።
ከህወሓት ውድቀት በኋላ ግን ይህ ዓይነት አካሄድ በድጋሚ ሊደገም እንደማይገባ አጽንኦት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ትግራይ የአንድ ድርጅት ርስት አትሆንም ሲሉ አስገንዝበዋል።
በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያለው ዲሞክራሲያዊ ነፃነት በትግራይም መረጋገጥ እንዳለበት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ፤ የሕዝቡን አንድነት ለማረጋገጥ መንግሥት በበኩሉ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ሁሉም አካባቢዎች በሕወሓት ሥር ከባድ መከራና ጭቆና እንደነበረባቸው ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ የፌዴራል መንግሥቱ ለሁሉም አካባቢዎች በእኩልነት እንደሚሠራና የትግራይም ልማት እንደሚመጣ ሙሉ እምነት እንዳላቸው አረጋግጠዋል።
በታደሰ ሽፈራው