የስጋ ዋጋ በሚስተካከልበት ሁኔታ ከስጋ ቤት ባለቤቶች ጋር ውይይት ተደረገ

You are currently viewing የስጋ ዋጋ በሚስተካከልበት ሁኔታ ከስጋ ቤት ባለቤቶች ጋር ውይይት ተደረገ

AMN – ጥቅምት 11/2019 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከስጋ ቤት ባለቤቶች ጋር ባደረገው ውይይት ስጋ ቤቶቹ በማህበራቸው አማካይነት ተወያይተው የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርጉ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅና የአዲስ አበባ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በጋራ በመሩት የወይይት መድረክ ፣ ከስጋ ቤቶች የዋጋ ጭማሪ አንፃር የተካሄደ ዳሰሳ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ከእርድ ከብት ጋር ተያይዞ በግብይት ሂደት የሚታዩ የደላላ ጣልቃ ገብነት ችግርን በማንሳት መንግስት እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።

ከእርድ ከብት አቅርቦት አንፃር ችግር ሳይኖር ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ሊኖር አይገባም ያሉት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ የስጋ ዋጋ የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በመዲናዋ በሚገኙ አምስት የቁም ከብት የገበያ ማዕከላት ላይ አርሶአደሩ ምርቱን በቀጥታ ይዞ እንዲቀርብ በማድረግ የስጋ ቤቶች የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በስጋ ዙሪያ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በዘርፉ እሴት የማይጨምሩ ህገ-ወጥ ደላላዎችን ከገበያው የማስወጣትና ሌሎች የቁጥጥር ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል።

በቀጣይ ከግብር፣ ከንግድ ፍቃድ አንፃር የቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ፣ የልኳንዳ ማህበራት ተወያይተው አሁን ያለውን ንረት ታሳቢ ያደረገ የዋጋ ተመን እንዲያወጡ አሳስበዋል።

በመጨረሻም የስጋ ቤት ባለቤቶች በማህበራቸው አማካይነት ተወያይተው በአጭር ጊዜ የዋጋ ማስተካከያ አድርገው እንዲያሳውቁ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review