AMN- መስከረም 9/2019 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ “ሰላማዊ መማር ማስተማር ለጋራ አብሮነት!” በሚል መሪ ሀሳብ ከትምህርት አመራሮች፣ ከሰላምና ጸጥታ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ እና ደንብ ማስከበር አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል አስራት ዴኔሮ፣ ተማሪዎች በትምህርታቸው በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ መሆን የሚችሉት ትምህርት ቤቶች ፍጹም ሰላማዊ የሆነ የመማር ማስተማር ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ሲችሉ መሆኑን አንስተዋል።
አያይዘውም በትምህርት የሚገነባው ትውልድ ሀገርን የሚገነባ እንዲሆን በስነ-ምግባር ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ሳምሶን መለሰ በበኩላቸው፣ በ2019 የትምህርት ዘመን ትምህርት ቤቶች ከማንኛውም ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ተጽዕኖ ነጻ ሆነው እንዲቀጥሉ ማገዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
አቶ ሳምሶን አክለውም የተማሪዎችን ውጤትና ስነ-ምግባር የማሻሻል ተልኳቸውን ማሳካት እንዲችሉ ሁሉም ባለድርሻ አካል ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩም “ሰላማዊ መማር ማስተማር ለጋራ አብሮነት!” በሚል የተዘጋጀ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ በጥልቀት ውይይት እየተካሄደበት ይገኛል።
በወንድምአገኝ አበበ