AMN- ኅዳር 17/2019 ዓ.ም
በ7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በከተሞች እየተገነባ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሆነ መሆኑን ተናግረዋል።
ዓለም ላይ 80 በመቶ የሚሆነው ኢኮኖሚ ከተማ ውስጥ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያም ከግማሽ ያላነሰው ኢኮኖሚዋ በአዲስ አበባ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ኢኮኖሚ የበለጠ ለማሳደግ ትልቅ እግዛ እያደረገ እንደሚገኝ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሥራው ለኢትዮጵያ በረከት ነው ብለዋል።

በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ወንድሞቻችን መቼ ነው ለእኛም ሚደርሰን የሚል ጥያቄ የሚያነሱለት የኮሪደር ልማትን ማራከስ እንደማይገባም አስገንዝበዋል።
የኮሪደር ልማት የመጣው ሰው ለማፈናቀል ነው በሚል የሚነሱ ስሞታዎችንም ተገቢ አለመሆናቸውን አስረድተዋል።
አዲስ አበባ ላይ ሰው ለማፈናቀል ከተባለ በሌሎች ከተሞችስ የሚሰሩ የኮሪዳር ልማቶች ለምንድነው? ሲሉ በመጠየቅ ስሞታውን መሰረተ ቢስ እንደሆነ አሳይተዋል።
በስንፍና የተሞሉ በሀገር እድገት ላይ ጋሬጣ የሆኑ ስሞታዎች አይጠቅሙም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “የኢትዮጵያ የከተሞች የኮሪደር ስራ የሚናናቅ ሳይሆን፣ በእያንዳንዱ አፍሪካ ሀገር ትልቅ ምኞት እና ቅናት ነው” ሲሉም ገልፀውታል።
የኮሪደር ልማት የሚገነባው ለሀገር እድገት እና ለመጪው ትውልድ እንደሆነ በመግለጽም፣ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
መንግስት የሚናገር፣ የሚያቅድ እና የሚገነባ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ክፍተቶች ሲኖሩ ተጋግዞ መስራት የበለጠ እድገታችንን ያፋጥነዋል ሲሉም ተናግረዋል።
በሸዋንግዛው ግርማ