የአዲስ አበባ አዲስ ገጽታና የብስክሌት ባህል

You are currently viewing የአዲስ አበባ አዲስ ገጽታና የብስክሌት ባህል

AMN – ሚያዝያ 10/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ በታሪኳ አይታው የማታውቀውን የከተማ ውበትና የመሠረተ ልማት ለውጥ እያስተናገደች ትገኛለች።

ከእነዚህ ለውጦች መካከል ደግሞ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው ለሰው ልጅ ምቾትና ለጤና ተስማሚ የሆኑ የኮሪደር ልማቶች መገንባታቸው ነው።

ይህ ልማት ደግሞ በከተማዋ ለዘመናት ተዘንግቶ የቆየውን የብስክሌትና የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎችን (ስኩተሮችን) ባህል ዳግም እንዲያንሰራራ እያደረገው ይገኛል።

እስከ አሁን ድረስ ብስክሌት በአዲስ አበባ ለብዙሃኑ እንደ መዝናኛ ወይም እንደ ስፖርት ብቻ ይታይ ነበር ፣ ይህም ቢሆንም በስፋት የሚዘወተር አልነበረም፤ አሁን ግን ይህ ልማድ እየተቀየረ ነው።

እንደ “አዲስ ባይክ” ያሉ ድርጅቶች ቴክኖሎጂን በመጠቀም የብስክሌት ኪራይ አገልግሎትን ለነዋሪው እያቀረቡ ይገኛሉ።

በመስቀል አደባባይ ሞተር አልባ ተሸከርካሪዎችን የሚያከራየው ሐቢብ ተጠቃሚዎች የ”አዲስ ባይክ” መተግበሪያን በማውረድና በፋይዳ ቁጥራቸው በመመዝገብ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ይገልጻል።

ለአንድ ጉዞ መነሻ 5 ብር ሲሆን፣ በደቂቃ ደግሞ 1 ብር እየታሰበ ደንበኞች በፈለጉት ፍጥነት ወደ መዳረሻቸው መጓዝ እንደሚችሉ ነው ሀቢብ የሚጠቅሰው።

ብስክሌቱን ከአንድ ቦታ ተከራይቶ መድረሻ ጋር፣ ለምሳሌ ባምቢስ፣ ወሎ ሰፈር ወይም ቦሌ ባሉ ጣቢያዎች ማቆም ይቻላል ።

የኮሪደር ልማቱ ለብስክሌተኞችና ለእግረኞች የሰጠው ልዩ ትኩረት የከተማዋን ነዋሪዎች የአኗኗር ዘይቤ እየቀየረ ነው።

በመስቀል አደባባይና አካባቢው የሚገኙ የብስክሌት ተጠቃሚዎች እንደሚሉት፣ አዲሱ መንገድ ሳይክል ለመጋለብ እጅግ ምቹ ከመሆኑም በላይ እንደ ስፖርትም እያገለገላቸው ይገኛል።

“ቅርብ ቦታ የምትሰራ ከሆነ ሌላ ወጪ ሳታወጣ ደርሰህ ትመለሳለህ” ሲል ነው በስፍራው በስክሌት ሲገለገል ያገኘነው ተጠቃሚ ጠቀሜታውን የገለጸው።

አዲሱ ለውጥ ወጣቶችንና አዋቂዎችን ብቻ ሳይሆን ህጻናትንም ጭምር የደስታ ተካፋይ ያደረጋቸው ሲሆን፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በስኩተርና በብስክሌት እያጫወቱበት ይገኛሉ።

ልጃቸውን ለማዝናናት መስቀል አደባባይ ይዘው የመጡት ወይዘሮ ጽጌ መግራ “ድሮ ያላየነውን አሁን አየን ፣ ትውልዱ ደስ እያለው ነው የሚያድገው” ሲሉ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

ህጻናትም በአዲሱ መንገድ ላይ በስኩተሮቻቸው ሲንሸራሸሩ የሚሰማቸው ደስታ ልዩ ነው።

የኬጂ ተማሪዋ ዮምናህ መሐመድ ስኩተር መንዳት በጣም እንደምትወድና አሁን ባለው ሁኔታ ትልቅ ደስታ እየተሰማት መሆኑን ገልጻለች።

ለዚህም እድል ስላበቃቻት እናቷን “እናቴ አመሰግንሻለሁ፤ እዚህ ስላመጣሽኝ አመሰግንሻለሁ” ስትል በልጅነት አንደበቷ ምስጋናዋን አቅርባለች።

ከመዝናኛና ከትራንስፖርት ባለፈ ይህ ዘርፍ ለበርካታ ወጣቶች አዲስ የገቢ ምንጭ እየሆነ እንዳለና ወጣቶች ስኩተሮችንና ብስክሌቶችን ለዕቃ ማድረሻ አገልግሎት በማዋል እንዲሁም በማከራየት ራሳቸውን እየደገፉ እንደሚገኙም ተገልጿል።

አዲስ አበባ አረንጓዴ ፣ ጤናማና ዘመናዊ የትራንስፖርት አማራጭ ያላት ከተማ ለመሆን በምታደርገው ጉዞ፣ ብስክሌትና ስኩተሮች የፊት ረድፉን ይዘዋል፣ ይህ ጅማሮ የከተማዋን ውበት ብቻ ሳይሆን የነዋሪዎቿንም መንፈስ እያደሰ ይገኛል።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review