ባል መሆን ትልቅ የኃላፊነት ስንቅ ነው!

You are currently viewing ባል መሆን ትልቅ የኃላፊነት ስንቅ ነው!

AMN-ሚያዝያ 10/2018 ዓ.ም

ዛሬ ዓለም አቀፍ የባሎች ቀን ነው ። ይህ ቀን ስለ ወንድነት ብቻ ሳይሆን፣ ስለ “ባልነት” ጥልቅ ትርጉም የሚታሰብበት ነው ፡፡

ብዙዎች ባል መሆንን ከስም ወይም ከማዕረግ ጋር ብቻ ያያይዙታል፤ ነገር ግን እውነተኛ ባልነት ከወንድነት በላይ መንፈሳዊ፣ ስነ-ልቦናዊ እና ማህበራዊ ዝግጅትን የሚጠይቅ ታላቅ ጥበብ ነው፡፡

ታዲያ ቀኑን ምክንያት በማድረግ የስነ-ልቦናና ጠቅላላ ሃኪም የሆኑትን ዶክተር ሰላም ዘገየን በጉዳዩ ሙያዊ ማብራሪያ ጠይቀን የሰጡንን ምላሽ እናጋራችሁ ፡፡

ባለሞያዋ እውነተኛ ባል ማነው? ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ ባል ማለት የአንድ ቤት ምሰሶ ብቻ ሳይሆን፣ የትዳር ተቋም ግንባታ መሃንዲስ ነው ፡፡

ዘንድሮ የባሎችን ቀን ስናከብር ዋና ትኩረታችን ሊሆኑ የሚገቡ ነጥቦችም መንፈሳዊና ስነ-ልቦናዊ ጥንካሬ አንዱ መሆኑን ነው ዶክተር ሰላም የሚገልፁት፡፡

ትዳር በትዕግስት፣ በይቅርታና በአርቆ አስተዋይነት የሚመራ ተቋም ነው። ለዚህ ደግሞ የውስጥ ሰላምና የተረጋጋ ስነ-ልቦና ቀዳሚው መስፈርት መሆኑን ጠቅሰዋል ፡፡ ሌላኛው ጊዜ መስጠት በትዳር ውስጥ ትልቁ ስጦታ ነው ፡፡

በስራ ቢወጠሩም፣ ለትዳር አጋር የሚሆን ጊዜ መመደብ የፍቅር መገለጫ ብቻ ሳይሆን የትዳር ዋስትና ነው፡፡ በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባር ለልጆቹና ለማህበረሰቡ የሚተርፍ መልካም ስብዕና ያለው፣ በስራ ባህሉ ጠንካራ የሆነና በፈተናዎች የማይናወጥ አርአያነት ያለው ሰው “ባል” ይሰኛል ሲሉ ባለሞያዋ ነግረውናል፡፡

በተለያዩ ሀገራት ስኬታማ የትዳር ህይወት ያላቸውን ወንዶች ስንመለከት ጥቂት የጋራ እሴቶችን እናገኛለን ያሉት ዶክተር ሰላም የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና ምሳሌዎች አጋርተውናል ፡፡

የአጋርነት ሚና (Partnership) በስካንዲኔቪያን ሀገራት (እንደ ዴንማርክ እና ኖርዌይ) “ባል” ማለት የቤት ውስጥ ስራንና የልጆች አስተዳደግን በእኩልነት የሚጋራ ማለት ነው።

ይህ አጋርነት ትዳርን ጠንካራና ደስተኛ ያደርገዋል፡፡ ሌላኛው ስሜትን የመግለጽ ብስለት በዘመናዊው ዓለም፣ ስኬታማ ባሎች ስሜታቸውን ለትዳር አጋራቸው በግልፅ የሚያጋሩና አድማጭ የሆኑ ናቸው፡፡

ይህም በትዳር ውስጥ ያለውን መተማመን (Emotional Intimacy) ያሳድገዋል፡፡ እንደ ባራክ ኦባማ ያሉ ታዋቂ ሰዎች ለትዳር አጋራቸውና ለቤተሰባቸው የሚሰጡት ክብርና ቅድሚያ፣ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንዶች አርአያ መሆናቸውን ዶክተር ሰላም በምሳሌነት አንስተዋል ፡፡

“ጠንካራ ቤተሰብ የጠንካራ ማህበረሰብ መሠረት ነው፤ ጠንካራ ቤተሰብ እንዲኖር ደግሞ የባሎች ሚና የማይተካ ነው!” እናም ሚስቶች ለባሎች የዕረፍት ቀን መስጠት ይህ ማለት ባልዎ በየቀኑ የሚያከናውናቸውን የቤት ውስጥ ሥራዎች ወይም የልጆች እንክብካቤ ዛሬ እርስዎ በመሸፈን ሙሉ ዕረፍት እንዲያገኝ ማድረግ።

የሚመርጡትን ልዩ የምግብ ዓይነት በማዘጋጀት በጋራ መመገብ። ትርፍ ጊዜን አብሮ ማሳለፍ እሱ የሚወዳቸውን የመዝናኛ ተግባራት (ለምሳሌ፦ ስፖርት መመልከት፣ ጨዋታዎችን መጫወት ወይም በእግር መጓዝ) አብሮ መሳተፍ ፡፡

ለሚያደርገው ጥረትና ለቤተሰቡ ላለው ቁርጠኝነት ያለዎትን አድናቆት በቃላት ወይም በጽሁፍ በመገለፅ አጋርነት ማሳየት እንደሚገባም ባለሞያዋ ገልፀዋል ፡፡

ስለሆነም ባል መሆን ክብር ነው፤ ለክብሩ የሚመጥን ማንነት መገንባት ደግሞ የሁልጊዜ ስራችን ሊሆን ይገባል የስነ-ልቦናና ጠቅላላ ሃኪም የሆኑት ዶክተር ሰላም ዘገየ መልእክት ነው።

ሚስቶች ለባሎቻችሁ የእንኳን አደረሰህ መልእክታችሁን በማጋራት ያላችሁን አድናቆት ግለፁላቸው ሲሉም መክረዋል።

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review