AMN – ሚያዝያ 11/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ሁሉም ዜጎች እኩል ተሳታፊ የሚሆኑበትና የአካል ጉዳተኞች መብት የተከበረበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ፍጻሜውን ሊያገኝ የ3 ቀናት ዕድሜ ብቻ ቀርተውታል።
አካታችነት የአንድ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዋነኛ መገለጫ እንደመሆኑ መጠን፣ በሀገሪቱ በሚካሄዱ የምርጫ ሂደቶች ውስጥ የአካል ጉዳተኛ ዜጎች ተሳትፎ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል።
እነዚህ ዜጎች በምርጫ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማረጋገጥና ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ለማስቻል ልዩ ልዩ የዝግጅት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸው ይታወቃል።
አቶ ፍጹም ተስፋዬ የተባሉት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አካል ጉዳተኝነት ሳይገድባቸው የሚመራቸውን አካል ለመምረጥ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸው፣ ሂደቱ ዘመናዊና ዲጂታል መሆኑ ለተሳትፏቸው ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

ሌላኛው ለመራጭነት ሊመዘገብ በምርጫ ጣቢያ የተገኘው ደረጀ ይልማ የተባለ አካል ጉዳተኛ በበኩሉ የሚበጀዉንና ለውጥ ያመጣል ብሎ ያመነበትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቱን በመግለጽ፣ የምርጫ ክርክሮቹ የሚፈልገዉን ፓርቲ ለመምረጥ ዕድል እንደፈጠረለት ተናግሯል፡፡
ይህ ሂደት አካታች በሆነ መልኩ መጠናቀቁ ለሀገሪቱ የዲሞክራሲ ጉዞ ትልቅ እምርታ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በወርቅነህ አቢዮ