AMN- ሚያዝያ 12/2018 ዓ.ም
አሜሪካ የኢራንን የንግድ መርከብ በቁጥጥር ስር ማዋሏን ተከትሎ፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሊፈርስ እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት ተፈጥሯል።
አሜሪካና እስራኤል ከኢራን ጋር የጀመሩት ግጭት 50ኛ ቀኑን ባስቆጠረበትና የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ሊጠናቀቅ የአንድ ቀን ዕድሜ ብቻ በቀረው በዛሬው ዕለት፣ ውጥረቱ ዳግም አንሰራርቷል።
ኢራን አሜሪካ በንግድ መርከቧ ላይ የፈጸመችውን ድርጊት “የታጠቁ የባሕር ላይ ዘራፊዎች ተግባር” ስትል የኮነነች ሲሆን፣ ይህንኑ ምክንያት በማድረግ በፓኪስታን ሊደረግ በታቀደው አዲስ የሰላም ንግግር ላይ እንደማትገኝ አስታውቃለች።
የአሜሪካ ወታደራዊ ማዕከላዊ ኮማንድ ባወጣው ተንቀሳቃሽ ምስል፣ የባሕር ኃይል ኮማንዶዎች በሄሊኮፕተር በመታገዝ ወደ ኢራን የንግድ መርከብ ሲወርዱ ታይተዋል።
መርከቧ በቁጥጥር ስር የዋለችው ለስድስት ሰዓታት ከዘለቀ ፍጥጫ በኋላ ሲሆን፣ የአሜሪካ የባሕር ኃይል በመርከቧ ሞተር ላይ በፈጸመው ጥቃት ከጥቅም ውጪ ካደረጋት በኋላ መሆኑ ተገልጿል።
ቴህራን በበኩሏ፣ መርከቧ ከቻይና ወደ ኢራን እየተጓዘች እንደነበር በመጥቀስ፣ በአሜሪካ የተፈጸመባትን ጥቃት ለመመከት ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባቃይ፣ ድርጊቱ ዋሽንግተን ለዲፕሎማሲያዊ ሂደቱ ቁርጠኛ አለመሆኗን የሚያሳይ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም፣ ኢራን በብሔራዊ ጥቅሟ ላይ ለሚሰነዘር ማንኛውም ማስፈራሪያ እጅ እንደማትሰጥና አሜሪካ የምታቀርባቸውን “ተቀባይነት የሌላቸው” ጥያቄዎች እንደማትቀበል አረጋግጠዋል።
ይህን ክስተት ተከትሎ በተፈጠረው አለመረጋጋት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በ6 በመቶ የጨመረ ሲሆን፣ የዓለም አቀፍ የአክሲዮን ገበያም መዋዠቅ አሳይቷል።
ዓለም አቀፍ የንግዱ ማኅበረሰብ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከፈረሰ፣ በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በኩል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ ሙሉ በሙሉ ሊቆም ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት እንዳደረባቸው መገለጹን ሮይተርስ ዘግቧል።
በወርቅነህ አቢዮ