AMN – ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም
የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት አረጋውያንንና አካል ጉዳተኛ ዜጎችን ከአላስፈላጊ እንግልት እየታደገ ይገኛል፡፡
አቶ ካሳሁን በቀለ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው፡፡ ለረጅም ጊዜ መታወቂያቸውን ለማሳደስ “መቼ ልሂድ?” እያሉ ሲያመነቱ ቆይተዋል፡፡
አንድ ቀን ግን ድንገት ከቤት እንደወጡ አዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በደጃፋቸው ተመልክተው ወደ አገልግሎት መስጫው ጎራ ያሉት አቶ ካሳሁን ቀደም ሲል በመንግስት መስሪያ ቤቶች ከአንድ እስከ ሁለት ወር ይፈጅባቸው የነበረውን የመታወቂያ እደሳት በአምስት ደቂቃ ብቻ ማጠናቀቃቸውን ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል፡፡

እዚሁ ደጃፌ ላይ መጥቶ በአምስት ደቂቃ ውስጥ አገልግሎት ማግኘት ትልቅ ለውጥ ነው፤ በጣም ደስ የሚል የአገልገሎት አሰጣጥ መሻሻል አንድ እርምጃ ጉዞ እየሄድን ነው ሲሉ ለውጡን አድንቀዋል፡፡
የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት እንደ መታወቂያ እና መንጃ ፍቃድ ያሉ አገልግሎቶችን ወደ ህብረተሰቡ ደጃፍ በማምጣት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ አሰራር በተለይ ለአረጋውያን፣አካል ጉዳተኞች እና በስራ ብዛት መንቀሳቀስ ለማይችሉ ዜጎች ትልቅ እፎይታ መፍጠሩን ገልጸው፤ መንግስት በዚህ መልኩ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ መስራቱ ከፍተኛ የለውጥ ምልክት መሆኑንም ተናግረዋል።

እንዲሁም በጦር ሀይሎች አካባቢ የሚገኙ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተንቀሳቃሽ አገልግሎቱ የነበረውን እንግልት እና ብልሹ አሰራር በማስቀረት የተገልጋዩን ድካም መቀነሱን ገልጸዋል፡፡
በአካባቢያቸው እንዲህ ያለ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸው የሀገር እድገትን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ፍኖት ተከትሎ የዘመነና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እና እውን ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ማሳያ ነው ፡፡
በትዝታ መንግስቱ