AMN- ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም
በሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስፋት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ማፋጠን እንደሚያስፈልግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የገንዘብ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማትን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃጸም ሪፖርት ገምግሟል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በሪፖርታቸው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዘንድሮው በጀት ዓመት 10 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችል ስኬት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በተሰራው ሥራም በታኅሳስ 2018 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የዋጋ ግሽበቱን ዘጠኝ ነጥብ ሰባት በመቶ በማድረስ ወደ አንድ አሃዝ ማውረድ መቻሉንና፤ የመጋቢት ወርም ወደ ዘጠኝ ነጥብ አራት በመቶ መውረዱን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት መንግስት ከብሔራዊ ባንክ ምንም ዓይነት ብድር አለመውሰዱን ጠቁመው፤ ከብሔራዊ ባንክ ቀጥታ የሚወሰደው ብድር እንዲቆም መደረጉ የዋጋ ንረት እንዲቀንስ አድርጓል ብለዋል።

በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ አማካኝነት ኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ እፎይታ እንድታገኝ ስኬታማ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ድርድር መደረጉንም ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ በጥብቅ የፊስካል ፖሊሲ ቁጥጥርና የቁጠባ ዲሲፕሊን በመመራቱ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ ዕድገት የምታስመዘግብ ሀገር እያደረጋት መሆኑን ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም፤ የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃጸም ሪፖርት መነሻ በማድረግ በዋጋ ግሽበት፣ የዕዳ ሽግሽግና ተያያዥ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ጥያቄና አስተያየት አቅርበዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በሰጡት ምላሽ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሚያስከትለውን ጫና ለመቀነስ በደመወዝ ጭማሪ፣ ማዳበሪያ፣ ነዳጅ፣ የምግብ ዘይትና መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ መንግስት ድጎማ እያደረገ ነው ብለዋል።

በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ በተደረጉ ስኬታማ ድርድሮችም ኢትዮጵያ ከጣሊያንና ፈረንሳይ የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት መፈረሟን አስረድተዋል።
ከቻይና ጋርም የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት መፈረም የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር ያለው ድርድር መቀጠሉን ገልጸዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ፤ ሪፖርቱ ቀጣይነት ያለው ዕድገት መኖሩን የሚያሳይ ነው ብለዋል።