የአብላጫውን የህዝብ ድምፅ ውጤት በመቀበል አሸናፊ ፓርቲዎች የገቡትን ቃል በተግባር እንዲፈፅሙ እንጠብቃለን – የመዲናዋ ነዋሪዎች

You are currently viewing የአብላጫውን የህዝብ ድምፅ ውጤት በመቀበል አሸናፊ ፓርቲዎች የገቡትን ቃል በተግባር እንዲፈፅሙ እንጠብቃለን – የመዲናዋ ነዋሪዎች

AMN-ግንቦት 27/2018 ዓ.ም

የለሊቱ ብርድ ሳይበግራቸው ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ የምርጫ ጣቢያዎችን ያጨናነቁት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በዘንድሮው ምርጫ ታሪክ ፅፈዋል።

እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ የዕድሜና የፆታ ልዩነት ሳይገድባቸው የወጡት እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች የነገዋን ሀገር ለመቅረጽ ረጅም ሰልፎችን አሳልፈው ለመምረጥ ችለዋል።

በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች የተሳተፉበት ይህ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ፣ ተራ የፖለቲካ ኩነት ሳይሆን የሰላማዊ ህይወት፣ የፍትሃዊነት እና የተሻለች ሀገር ፍለጋ ትልቅ ማሳያ ብቻም ሳይሆን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደትንም አሳይቶ አልፏል።

ከከተማ እስከ ገጠር ያሉ መራጮች የሀገራቸውን መፃኢ እድል ለመወሰን የምርጫ ካርዳቸውን ይዘው ረጅም ሰዓታት በትዕግስት ሲጠባበቁ ውለው አምሽተዋል።

በዚህ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ የነበሩት ዜጎች፣ በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ድምፃቸውን ካስመዘገቡ በኋላ ከምርጫው ማግስት የሚጠበቀውን ትልቅ ሀገራዊ ሀላፊነትም በስፋት እያነሱ ይገኛሉ።

በምርጫው የነቃ ተሳትፎ ያደረጉ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት፣ የዲሞክራሲ ውበቱና እውነተኛው ፈተና ምርጫው በሚጠናቀቅበት ቅጽበት የሚቆም ሳይሆን፣ ከምርጫው በኋላ የሚመጣውን የአብላጫውን ህዝብ የድምፅ ውጤት በፀጋ፣ በክብርና በታላቅ የሀገር ፍቅር ስሜት በመቀበል የሚገለፅ መሆኑን ኤ ኤም ኤን ዲጂታል ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ይህ የምርጫ ሂደት ማጠናቀቂያ ብቻ ሳይሆን አዲስ የኃላፊነት ምዕራፍ መጀመሪያ መሆኑን የህዝቡ አስተያየት ያረጋግጣል።

በምርጫው የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች በህዝብ ድምፅ አሸናፊው ለሚሆነው ፓርቲም ግልጽና ጠንከር ያለ መልዕክት ማስተላለፍን አልረሱም።

ነዋሪዎቹ በሰጡት አስተያየት፣ አሸናፊው አካል በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የገባውን ቃል ወደ ተግባር መተርጎም ያለበት ከዛሬ ጀምሮ እንደሆነ ይናገራሉ።

ህዝቡ የሰጠው እያንዳንዱ ድምፅ የተሻለ የኑሮ ሁኔታን፣ አስተማማኝ የሀገር ሰላምን፣ የስራ እድል ፈጠራንና የማህበራዊ ዘርፎችን እድገት የያዘ በመሆኑ፣ ስልጣን የሚይዘው አካል እነዚህን ጥያቄዎች በትኩረት የመመለስ ታሪካዊና የሞራል ግዴታ እንዳለበት በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review