AMN- ነሐሴ 8/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ህብረተሰቡ በከተማ ግብርና በስፋት እንዲሳተፍ እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ በከተማ ግብርና ጤንነቱ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ የግብርና ምርት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እየተደረገ ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ከከተማዋ እድገት ጋር አብረው እንዲለወጡ፣ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ከተማ ግብር ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባዩ ሽጉጤ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል፡፡
ምግቤን ከጓሮዬ በሚል መርህ የተጀመረው የከተማ ግብርና ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ሲሆን፤ ይሄም የከተማዋ ነዋሪ ሸማች ብቻ ሳይሆን አምራች መሆን የሚችልበትን ሁኔታ እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

በከተማ ግብርና የሚሳተፉ ነዋሪዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን በመግለጽ ስኬቱ ህብረተሰቡ ላይ ግንዛቤ በመፈጠሩ የመጣ ለውጥ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
ይሄም ግብርና በከተማ ላይ አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ የቀየረ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ባሉት ውስን ቦታዎች ላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና አሰራርን በመጠቀም ማምረት እንደሚቻል ማሳየት ተችሏልም ብለዋል፡፡
2 ሺህ 722 ተቋማት የግብርና ምርት ማምረቻ ማዕከል እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ከእነዚህ መካከል ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ይገኙበታልም ነው ያሉት፡፡
የሻምበል ምህረት