AMN- ሐምሌ 9/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መጥታ በጉባኤው ሂደት ላይ እያለች ለወለደችው ወጣት ክርኑዶ ኡጁሉ እንኳን በሰላም ተገላገልሽ በማለት ጠይቀዋታል፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ “ምንም እንኳን የመውለጃዬ ቀን ቢቃረብም “ሀገሬ ጠርታኝ አልቀርም” በማለት ከጋምቤላ ክልል ወደ አዲስ አበባ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የመጣችው ወጣት ክርኑዶ ኡጁሉ፣ በጉባኤው ሂደት ላይ እያለች በዘውዲቱ ሆስፒታል ወንድ ልጅ በሰላም ተገላግላለች ብለዋል።
የሀገር ፍቅር እና የእኔነት ስሜት ሲኖር የማይቻል ነገር አለመኖሩን ማሳያ የሆነችውን ይህችን ጀግና እናት፤ ከጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ ጋር በመሆን ባረፈችበት ቤት በመገኘት እንኳን ደስ አለሽ ብለናታል በማለትም ገልጸዋል።

ይህችው ጀግና እናት፤ የተለመደውን ስም የማውጣት ባህል በመተው፣ የልጇን ስም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እንዲያወጣላት በጠየቀችው መሰረት የህፃኑን ስም “ምክክር” ብላዋለች ሲሉም አክለዋል።
ዛሬም በሄድንበት ወቅት፣ ወጣቷ የመጣችበትን ታላቅ ሀገራዊ ዓላማ ለማሳካት ከጥቂት ቀናት እረፍት በኋላ ወደ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በልበ ሙሉነት እንደምትመለስ አረጋግጣልናለች ብለዋል።
እኛም ጉባኤውን አጠናቃ ወደ መጣችበት እስክትመለስ ድረስ ለእሷና ለልጇ የሚያስፈልገውን ድጋፍ እናደርግላታለን።
እህታችን ወንድ ልጇን በሰላም ተገላግላ በደስታ እንደተሞላች ሁሉ፤ ኢትዮጵያ ሀገራችንም ከገጠማት አንዳንድ ችግሮች በምክክር እና በንግግር ተገላግላ፣ ትልቅ እና ወሳኝ የሽግግር ምዕራፍ እንደሚሆንላት ፅኑ እምነታችን ነው።

ህፃን ምክክርም፤ እደግ ተመንደግልን! አንተ እና መሰል የኢትዮጵያ ህፃናት ሁሉ ቦርቃችሁ እና ተደስታችሁ የምታድጉባት፣ እንዲሁም የምትረከባት ሀገር ሰላሟ ሙሉ የሆነች፣ የህዝቦች ፍቅር ያበበበት እና የበለፀገች ኢትዮጵያ እንድትሆን ከልብ እንመኛለን በማለትም መልዕክት አስተላልፈዋል።