AMN- ግንቦት 6/2018 ዓ.ም
መራጮች በድምፅ መስጫ ቀን በምርጫ ጣቢያ ሲገኙ በሁለት የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ድምጻቸዉን ይሰጣሉ፡፡
በድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ድምጽ በሚሰጡበት ወቅትም የድምጽ አሰጣጥ መመሪያዉን በአግባቡ በመከተል ምልክት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ ሁለት የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን አዘጋጅቷል፡፡ እነሱም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ድምጽ መስጫ ወረቀት እና የክልል ምክር ቤት ዕጩ የድምጽ መስጫ ወረቀት ናቸዉ፡፡
መራጮች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ አንድ ዕጩ ብቻ የሚመርጡ ሲሆን በክልል ምክር ቤት ዕጩ የድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ ደግሞ አንድና ከዚያ በላይ ዕጩ መምረጥ ይችላሉ፡፡

ዕጩ ተወዳዳሪዎችን በሚገልጸዉ የድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ የዕጩ ተራ ቁጥር፣ የዕጩ ፎቶ፣ የዕጩ ምልክት፣ የመረጡትን ዕጩ ምልክት በማድረግ የሚያሳዩበት ሳጥን፣ የዕጩ እና የፖለቲካ ፖርቲ ስም ተካቶበታል፡፡
በምርጫው እለት ድምፅ ለመስጠት በዕጩው ስም ትይዩ ባለው ባዶ ሳጥን ውስጥ ብቻ ምልክት ማድረግ እንደሚገባ ያሳሰበው ቦርዱ፣ ተቀባይነት ያላቸውን የምልክት ዓይነቶችም በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
መራጮች የመረጡት ዕጩ በሚገኝበት ሳጥን ዉስጥ በእስክሪብቶ ወይም በጣት አሻራ ምልክት ያደርጋሉ፡፡
መራጮች የሰጡት ድምጽ ዋጋ እንዲኖረዉ በድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ የተጠቀሱትን መመሪያዎች በመከተል ምልክት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸዉ ቦርዱ አስታዉቋል፡፡
መራጮች ለበለጠ መረጃ የቦርዱን ድረ-ገጽ (www.nebe.org.et) ወይም የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን መጠቀም እንደሚችሉ ቦርዱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአስማረ መኮንን