AMN- ግንቦት 7/2018 ዓ.ም
የትውልድ ጽምጽ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ተወዳዳሪና ተመራጭ የመዲናዋ የመረጃ ቋትና ልሳን በመሆን ህዝቡን በግንባር ቀደምነት እያገለገለ መሆኑን የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤው የሾማቸዉ አዲስ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በተቋሙ በመገኘት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግመዋል።
በግምገማው ተቋሙ ምቹ ባልሆነ የሥራ አካባቢ ውስጥ ሆኖ ተመራጭና ተደማጭ መረጃዎችን በማድረስ የህዝብ ሚዲያነቱን በተግባር ማረጋገጡን አድንቀዋል።
የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻ፤ ተቋሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸው የይዘትና የአቀራረብ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም ተቋሙ በሀገር ውስጥ ካሉ የግልና የመንግስት ሚዲያዎች አንጻር ተመራጭ መሆን ብቻ ሳይሆን ከመዲናዋ የስበት ማዕከልነት እኩል የሚጓዝ ስርዓት ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል፡፡
የሥራ አመራር ቦርድ አባል ሚኤሳ ኤሌማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የሚዲያ ሪፎርሙ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው በጥራት፣ በብዛትና በአዋጭነት የሪፎርም ሂደቱን ቀጣይነት ለመጠበቅ በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የሥራ አመራር ቦርድ አባል ወ/ሮ ዘሀራ መሐመድ፤ ተቋሙ ፍጥነትን፣ በቡድን መስራትንና ተአማኒነትን ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑ በግልጽ ታውቋል ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ተቋሙ ‘ሜትሮፖሊታን ሚዲያ’ የመሆን ራዕይ እንዳለው ያስታወሱት የቦርድ አባል አቶ ሰለሞን ካሳ፤ ዓለም አቀፍ ተደራሽነትን ለማስፋፋት በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዘ አሰራር መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ዲባባ በበኩላቸው፤ ተቋሙ በተለያዩ ይዘቶችና አቀራረቦች ብቻ ሳይሆን በላቀ የቴክኖሎጂ ልማትና የአሰራር ስርዓት ተመራጭ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም ተቋሙ ለከተማዋ ሁለንተናዊ እድገትና ለሀሳብ ነጻነት የሚተጋ፣ ከልማቱና ከለውጡ እኩል የሚጓዝ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን በትጋት እየሰራ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው አመልክተዋል።
የአፍሪካ መዲናና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባን የሚመጥን ተቋም ለመገንባት፣ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል የጠነከረ ምህዳር መፍጠር እንዲሁም ዘመኑን የሚዋጁ አዳዲስ ፕሮግራሞችን መቅረጽ በቀጣይ በትኩረት የሚሰራባቸው ዋና ዋና አቅጣጫዎች መሆናቸውን የቦርድ አባላት ጠቁመዋል።
በትዝታ መንግስቱ