AMN – ግንቦት 12/ 2018 ዓ.ም
በአሁኑ ዘመን “ስማርት ሲቲ” ወይም “ብልህ ከተማ” ማለት የረጃጅም ህንፃዎች መኖር ሳይሆን፣ ቴክኖሎጂን ከዕለት ተዕለት የነዋሪዎች ህይወት ጋር በማቀናጀት አገልግሎትን ማዘመንና የሀብት ብክነትን መቀነስ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ዋናው ግቡም መረጃዎችን በቀጥታ በመሰብሰብ እንደ ትራፊክ፣ የኃይል አቅርቦት፣ የቆሻሻ አወጋገድ እና የህዝብ ደህንነት ያሉ የከተማ መዋቅሮችን በብልሃት መምራት ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ይህንን እውን ለማድረግ የዓለም አቀፍ “የእህት ከተሞች” ትስስርን እንደ ቴክኖሎጂ ሽግግር ድልድይ በመጠቀም፣ የወረቀት ላይ ስምምነቶችን በተጨባጭ ወደ መሬት እያወረደ ይገኛል፡፡

መዲናዋ ከአውሮፓዋ ሊዮን ከተማ ጋር ካላት በርካታ አመታትን ያስቆጠረ ትስስር በተገኘ ልምድ፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ሰፊ የኮሪደር እና የወንዞች ዳርቻ ልማት እየተተገበረ ይገኛል።
በአዲስ አበባ አዳዲስ የእግረኛ መንገዶች እና የብስክሌት መስመሮች መገንባታቸውም የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ የአየር ጥራትንና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን አሳድጓል።
የአዲስ አበባ እህት ከተማ የሆነችው ኪጋሊ አገልግሎቶችን 100% ዲጂታላይዝ በማድረግ ቀዳሚ ከተማ መሆኗ ይታወቃል። አዲስ አበባም ይህንን ተሞክሮ በመውሰድ ወረቀት አልባ አሰራርን፣ ዲጂታል መታወቂያን እና የተሳሰረ የህክምና መዝገብን ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች፡፡
በዚህም የወሳኝ ኩነት፣ የንግድ ፈቃድ እና የቤት ግብር ክፍያዎች በኦንላይን እንዲከናወኑ ተደርጓል።
የመንገድ ደህንነትን በቴክኖሎጂ ለመቆጣጠር እና የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ በተደረገው ትብብር አዲስ አበባ የብሉምበርግ ዓለም አቀፍ ሽልማትን አሸንፋለች።
አሁን ባለው የኮሪደር ልማትም በርካታ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ጣቢያዎች በቁልፍ ስፍራዎች ላይ ተገንብተዋል።
ከጓንግዙ፣ ቾንግቺንግ እና ሻንጋይ ከመሳሰሉ እህት ከተሞች በተገኙ ተሞክሮዎች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የታገዘ የከተማ ደህንነት ቁጥጥር እና የ5G መሰረተ-ልማት ዝርጋታ ውጤት አስገኝቷል።

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች እና አካባቢዎች ላይ የተገጠሙት ዘመናዊ የሲሲቲቪ (CCTV) ካሜራዎች እና ስማርት የትራፊክ መብራቶች የዚሁ ቴክኖሎጂ ማሳያ ናቸው።
ሌላው የአዘርባጃኗ ባኩ ከተማ በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁሉንም የመንግስት አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል በዲጂታል በሚያቀርበው የ”አሳን” (ASAN) አገልግሎት አሰጣጥ የታወቀች ከተማ ናት፡፡
ሰሞኑን ከባኩ ከተማ ጋር በተደረገው አዲስ የእህትማማችነት ስምምነት መሰረት፣ አዲስ አበባ የህዝብ አገልግሎቶችን ይበልጥ ዲጂታላይዝ ለማድረግ የባኩን የ”አሳን” አሰራር ልምድ ወደ ከተማዋ አስተዳደር ለማስገባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የ”ስማርት ሲቲ” ጉዞ አጋር ከተሞች ያካበቱትን የዓመታት ስኬታማ ልምድ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማቀናጀት በተጨባጭ መሬት ላይ መታየት ጀምሯል።
በኮሪደር ልማቱ ላይ የሚታዩት ዘመናዊ የእግረኛ መንገዶች፣ የኤሌክትሪክ መኪናዎች መሙያ ጣቢያዎች፣ የካሜራና ቴክኖሎጂ ትስስር እና የወረቀት አልባ አሰራር ሙከራዎች ከተማዋ ወደ ተሟላ “ብልህ ከተማነት” ለምታደርገው የነገ ጉዞ አስተማማኝ ማሳያዎች ናቸው።
በአስማረ መኮንን