የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ እና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻውን እየተወጣ ነው

AMN- ግንቦት 15/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ እና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የማህበሩ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ እናትአለም እንዳለ ገለጹ፡፡

ማህበሩ ከሴት የማህበሩ አባላት ጋር በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ ምክክር ያደረገ ሲሆን፣ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ማህበሩ ከተመሰረተ 28 ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ ከዚህ በፊት ካካበተው ልምድ በመነሳትም በምርጫ ሂደቱ ላይ የራሱን አሻራ እያሳረፈ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

በውይይቱ ላይ እንደተነሳው፣ ሴቶች በሀገራዊ ውሳኔዎች ላይ የመወሰንና የመሳተፍ መብታቸው ሊከበር ይገባል፤ ይህም ምርጫው የሴቶችን ድምፅና ተሳትፎ በላቀ ደረጃ የሚያንጸባርቅ መሆን ይገባዋል።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ እናትአለም እንዳለ እንደገለጹት፣ ማህበሩ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆኖ፣ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ማህበሩ በከተማዋ በሚገኙ ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች አማካኝነት ከሴት አባላቱ ጋር በመወያየት፣ በምርጫ ወቅት ችግሮች እንዳይከሰቱ ለመከላከል እና የሰላም ግንባታ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑ ተመልክቷል።

ሴቶች በምርጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ያለውን ሚና አጠናክሮ የቀጠለው ማህበሩ፣ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ማህበሩ አስታውቋል።

በጽዮን ማሞ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review