AMN – ግንቦት 14 / 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሳንዶካን ደበበ፣ በኒውክሊየር ዘርፍ ስትራቴጂካዊ ትብብር ዙሪያ ለመምከር የመጡትን በቻይና አቶሚክ ኢነርጂ ባለስልጣን ምክትል ሊቀመንበር ሊ ጂንግ የተመራ የቻይና ልዑካን ቡድን በቢሮቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
የሁለትዮሽ ምክክሩ በኢትዮጵያ የሰው ኃይል ልማት እና በተቋማዊ አቅም ግንባታ ላይ በዋናነት ትኩረቱን በማድረግ ተካሂዷል።
በዘርፉ ቁልፍ የሆኑ የቴክኒክ ልምዶችን ለመለዋወጥ እና የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ስትራቴጂዎችን ለመቅረጽ የሚያስችሉ ሰፊ ውይይቶች መካሄዳቸውም ተገልጿል።
በኒውክሊየር ልማት ብቁ የሀገር ውስጥ ባለሙያ ለማፍራት እንዲቻል እና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች እና ለኮሚሽኑ ሰራተኞች የትምህርት ዕድልና የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሞችን ማመቻቸት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ስምምነት መደረሱን ኮሚሽኑ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አሳውቋል።

በተጨማሪም ኮሚሽነር ሳንዶካን እና የቻይናው ልዑካን ቡድን በተለይ በፋይናንሻል ሞዴሊንግ ልምዶች እና ጠንካራ ተቋማዊ አቅምን ለመገንባት በሚረዱ ስትራቴጂዎች ላይ ዝርዝር ምክክር አድርገዋል።
ምክክሮቹ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የኒውክሊየር ኃይል ዘርፍ ዘላቂ ማዕቀፎችን ለመዘርጋት፣ የቁጥጥር ደረጃዎችን ለማውጣት እና አስተማማኝ የፋይናንስ መንገዶችን ለመቅረጽ ለምታደርገው ብሔራዊ ጥረት እጅግ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ሚና እንዳለቸው ተገልጿል።
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የቻይና አቶሚክ ኢነርጂ ባለስልጣን ምክትል ሊቀመንበር ሊ ጂንግ ፣ የቻይና ብሔራዊ ኒውክሊየር ኮርፖሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ማ ዌንጁን እና በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ከፍተኛ ተወካዮች ተገኝተዋል።
ይህ ግንኙነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጥልቅ ስትራቴጂካዊ ትብብር የሚያንፀባርቅና በአቶሚክ ኃይል ሰላማዊ አጠቃቀም ረገድ ለወደፊት የጋራ ፕሮጀክቶች እና ለዘላቂ የሁለትዮሽ ግንኙነት አዲስና ብሩህ መንገድ የሚከፍት መሆኑን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል።