በምሥራቅ ሸዋ ዞን የተጀመሩ የልማትና የኢንቨስትመንት ንቅናቄዎች የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥኑ ናቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶር)

You are currently viewing በምሥራቅ ሸዋ ዞን የተጀመሩ የልማትና የኢንቨስትመንት ንቅናቄዎች የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥኑ ናቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶር)

AMN – ግንቦት 15/ 2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶር) በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሸዋ ዞን በገጠርና በከተማ የተጀመሩ የተቀናጁ የልማት ሥራዎች፣ የግብርና ማዘመን ንቅናቄዎችና የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች የሕዝቡን የኢኮኖሚና የገቢ ችግር ከመሠረቱ ከመቅረፍ ባለፈ፣ የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥኑ መሆናቸውን ገለጹ።

በሞጆ ከተማ የተመረቀው አዲስ ፋብሪካም የአካባቢውን ታሪካዊ የኢንዱስትሪ መናኸሪያነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን አንስተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ልዩ ልዩ ወረዳዎች የተካሄደውን የመስክ ምልከታና የፋብሪካ ምረቃ አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ የተጀመሩ ስትራቴጂካዊ ንቅናቄዎች አሁን ላይ ተጠናክረው በመቀጠላቸው ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።

ይህ ስኬት እንዲሁ ሳይሆን በተግባር የተረጋገጠ እና መሬት የረገጠ ሥራ መሆኑን በመግለጽም ዘርፉ የሕዝቡን የኢኮኖሚና የገቢ ችግር ከመሠረቱ መፍታት እንደሚችል ማሳያ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ምሥራቅ ሸዋ በቀን ከ10 እስከ 20 ሚሊዮን እንቁላል የማምረት ሰፊ አቅም ያለው አካባቢ ሲሆን፣ ከዚህ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በትላልቅ ፋብሪካዎች ከሚመረት ምርት እኩል ከፍተኛ የገንዘብ ፍሰት የሚያስገኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

በተጨማሪም በአካባቢው በቀን ከ10 እስከ 20 ሚሊዮን ሊትር ወተት ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ያለ ሲሆን፣ ይህንን እውን ማድረግ ከተቻለ የሚገኘው አጠቃላይ ገቢ ከትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የማይተናነስ መሆኑን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ ቅኝት እና ምልከታ ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት፣ እየተካሄደ ያለው የግብርና እንቅስቃሴ አበረታች ቢሆንም አሁንም በባህላዊና በዘመናዊ አሠራር መካከል ክፍተቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ከፊሉ አርሶ አደር በትራክተር እያረሰ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ከፊሉ ደግሞ አሁንም በበሬ የሚያርስበት ሁኔታ ይስተዋላል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁንም ሕዝባችን በበሬ በሚያርስበት ሁኔታ፣ መተኛት፣ መደሰትና ሠራን ብሎ ማሰብ ከእኛ የሚጠበቅ አይደለም፤ አሁን ክረምት እየመጣ ነው፤ ገበሬው ሕዝባችን ከዚህ ባህላዊ አሠራር ወጥቶ ሙሉ በሙሉ ማሽነሪዎችን እንዲጠቀምና ምርታማነቱ እንዲያድግ ከእኛ የሚጠበቀው ሥራ በጣም ብዙ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።

በምሥራቅ ሸዋ ዞን ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች እየተገነቡና እየዘመኑ ያሉ የመሠረተ ልማት አውታሮች የሕዝቡን የኑሮ ዘይቤ እየቀየሩ ይገኛሉ። እየተከናወኑ ያሉ የላቁ የልማት ሥራዎች በአንድ በኩል “እስከ አሁን ለረጅም ዘመን በዚህ መልኩ እንዴት ተኝተን ነበር?” የሚያሰኙና ሥራዎቹ ከ10 እና 20 ዓመታት በፊት ተጀምረው ቢሆን ኖሮ የሕዝቡ የዕድገት ደረጃ ዛሬ የት በደረሰ ነበር የሚል ጥያቄ የሚያስነሱ ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በሌላ በኩል ደግሞ አሁን የተጀመረውን ትልቅ ሥራ እንደ ትልቅ ስኬት ቆጥሮ ወደ መተኛት፣ መላላትና መድከም ካመራን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ኋላ ልንመለስ እንደምንችል የሚያሳዩ ተጨባጭ ሁኔታዎች እንዳሉም ተጠቁሟል።

በተለይም የተገነቡ ዘመናዊ መንገዶችን በተመለከተ አሽከርካሪዎችና የሚመለከታቸው አካላት መንገዱ ስንት ኪሎ ሜትር እንደሆነ፣ ጥራቱ ምን እንደሚመስልና መንግሥት ምን ያህል ከፍተኛ ወጪ እንዳወጣበት ለሕዝቡ ሊያብራሩ እንደሚገባ ተገልጿል።

ይህ መንገድ ሞጆንና አዳማን ይዞ ሲዘልቅ የሚፈጥረውን የኢኮኖሚ ትስስር መረዳት እጅግ አስፈላጊ መሆኑም ተመልክቷል።

በሞጆ ከተማ የተመረቀውን አዲስ ፋብሪካ አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ እንግዶች በፋብሪካውና በሞጆ ከተማ መካከል ያለውን ጠንካራ ትስስር ለመረዳት ሊቸገሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስለ ፋብሪካና ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ሲነሳ ሞጆ ስሟ ቀድሞ ከሚነሳባቸው ጥቂት የፋብሪካ ከተሞች መካከል ግንባር ቀደሟ መሆኗን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በምሥራቅ ሸዋና በሙሉ ሸዋ የጀመራቸው የተቀናጁ የልማት ሥራዎች ስኬት ካገኙ፣ ኢትዮጵያ ልክ እንደታሰበው ብልጽግናን ለማረጋገጥ፣ ከልመናና ከዕርዳታ ጥገኝነት ለመውጣት፣ እንዲሁም ሌሎች ሀገራትን ጭምር ለመርዳት የሚያስችል ትልቅ አቅም ያላት ሀገር መሆኗን በተግባር ማረጋገጥ እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review